በኮሮና ቫይረስ የተያዙ ሰዎች ቁጥር ከአምስት ሚሊዮን አለፈ፡፡

183

ባሕር ዳር፡ ግንቦት 13/2012 ዓ.ም (አብመድ) የኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝ በአምስት ወራት ቆይታው በዓለማቀፍ ደረጃ ከአምስት ሚሊዮን የሚበልጡ ሰዎችን መያዙን የጆን ሆፕኪንስ ዩኒቨርሲቲ አስታወቀ፡፡

መረጃ እንደሚያመለክተው 5 ሚሊዮን 90 ሺህ 977 ሰዎች በቫይረሱ መያዛቸው ተረጋግጧል፡፡ በቫይረሱ ከተያዙት ውስጥ 329 ሺህ 757 ሰዎች ሕይወታቸው አልፏል፤ 2 ሚሊዮን 25 ሺህ 878 ደግሞ ከቫይረሱ አገግመዋል፡፡

የጆን ሆፕኪንስ ዩኒቨርሲቲ በየሀገራቱ ያልተመረመሩ በርካቶች መሆናቸውን በመግለጽ በቫይረሱ የተያዙትና ሕይወታቸው ያለፉት ከዚህም ሊያልፍ እንደሚችል አመላክቷል፡፡

የዓለም ጤና ድርጅት ደግሞ በቀን ከ100 ሺህ በላይ ሰዎች በቫይረሱ መያዛቸው ሪፖርት እየተደረገለት እንደሆነ በመግለጽ ሁሉም ጥንቃቄ እንዲያደርግ አሳስቧል፡፡

በተለያዩ ሀገራት መድኃኒትና ክትባት ፍለጋ ሩጫው ቢቀጥልም በቀላሉ ስኬት ላይ የሚደረስ አለመሆኑ እየተነገረ ነው፡፡ ክትባትና መድኃኒት ቢገኙ እንኳ በፍጥነት ለዓለም ሕዝብ ማዳረስ መቻሉ አጠያያቂ እንደሚሆን እየተገለጸ ነው፡፡

እስካሁን ፍቱን ሆኖ የተገኘው መከላከያ አካላዊ ርቀትን መጠበቅ፣ እጆችን በንጹሕ ውኃና በሳሙና በአግባቡ አሽቶ መታጠብ፣ ሲስሉና ሲያስነጥሱ አፍና አፍንጫን መሸፈን የሚሉት ምክረ ሐሳባች ናቸው፡፡

በአብርሃም በዕውቀት

Previous article1 ነጥብ 75 ቢሊዮን ችግኝ ለመትከል ዝግጅት መደረጉን የአማራ ክልል ግብርና ቢሮ አስታወቀ፡፡
Next articleበጎንደር ከተማ እየተከናወኑ የሚገኙ መሠረተ ልማቶች በተሻለ አፈጻጸም ላይ መሆናቸውን የሥራ ኃላፊዎች ተናገሩ፡፡