
ጎንደር: ግንቦት 04/2017 ዓ.ም (አሚኮ) “የጥፋት እጆች እና መዘዞቹ” በሚል መሪ መልዕክ የማዕከላዊ ጎንደር ዞን ከወጣቶች ጋር ውይይት አካሂዷል። በውይይቱ ላይ የአማራ ክልል የልህቀት ዲዛይን እና ቁጥጥር ሥራ ኮርፖሬሽን አማካሪ ፍቃዴ ዳምጤ (ዶ.ር)፣ የማዕከላዊ ጎንደር ዞን አሥተዳዳሪ አወቀ አስፈሬ፣ ከዞኑ የተውጣጡ ወጣቶች እና ሌሎች የሥራ ኀላፊዎች ተገኝተዋል።
በውይይቱ ላይ በአማራ ክልል በተከሰተው የሰላም እጦት ምክንያት የደረሰው ጉዳት በዝርዝር ቀርቦም ውይይት ተደርጎበታል። የክልሉ የሰላም እጦት ከፍተኛ ውድመት ማድረሱን የገለጹት ተሳታፊዎቹ የሰላም እጦቱ ወደነበረበት እንዲመለስ ሁሉም ሊሠራ ይገባል ብለዋል። በሰላም እጦቱ የማኅበረሰቡ እንቅስቃሴ መገደቡን ወጣቶቹ አንስተዋል።
የሰላም እጦቱን ተገን በማድረግ ሙስና እና ብልሹ አሠራር እየተስፋፋ እንደሚገኝም ተነስቷል። የመሬት ወረራም በስፋት እየተፈጸመ እንደሚገኝ ነው የተመላከተው። የሰላም እጦቱ ወደ መረጋጋት እንዳይመጣ “ከዚህም ከዛም” የሚረግጡ መሪዎች መኖራቸውን ያነሱት ወጣቶቹ ችግሮችን ለመሻገር የማኅበረሰቡ አንድነት እና መተባበር አስፈላጊ ነው ብለዋል።
የመንግሥት መዋቅሩም ቢኾን ከብልሹ አሠራር ራሱን በማራቅ ለሰላም መምጣት ቁርጠኛ ኾኖ ሊሠራ እንደሚገባ ተገልጿል። ወጣቶቹ ዘላቂ ሰላም እንዲሰፍን የበኩላቸውን እንደሚወጡም አረጋግጠዋል። በክልሉ የተፈጠረውን የሰላም እጦት ለመመለስ ወጣቱ አቅም እንዳለው የገለጹት የአማራ ክልል የልህቀት ዲዛይን እና ቁጥጥር ሥራ ኮርፖሬሽን አማካሪ ፍቃዴ ዳምጤ (ዶ.ር) ሰላም እንዲመጣ ወጣቶች መሥራት ይጠበቅባችኋል ብለዋል።
በብልሹ አሠራር ውስጥ የሚገኙ የመንግሥት መሪዎችን በማጋለጥ በኩልም ማኅበረሰቡ አጋዥ መኾን እንዳለበትም ነው የተናገሩት። ሰላምን ለማረጋገጥ መንግሥት የመንግሥትነቱን ድርሻ ይወጣል ያሉት የማዕከላዊ ጎንደር ዞን አሥተዳዳሪ አወቀ አስፈሬ ማኅበረሰቡ እንደማኅበረሰብ የራሱን ኀላፊነት ሊወጣ ይገባል ብለዋል።
መንግሥት ከሚያደርገው ሕግ የማስከበር ጎን ለጎን አካባቢያቸውን ነጻ በማድረግ በኩል በዞኑ የሚጠቀሱ አካባቢዎች መኖራቸውንም አቶ አወቀ ገልጸዋል። ታጥቀው ጫካ የገቡ ኀይሎች የሰላም አማራጭን እንዲጠቀሙ ጥሪ ማቅረብ እንደሚገባም ተናግረዋል። መንግሥት ከሚያቀርበው የሰላም አማራጭ ጎን ለጎን የሕግ ማስከበር ሂደቱን እንደሚያስቀጥልም ተገልጿል።
ዘጋቢ-ደስታ ካሳ
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን