በ185 ሚሊዮን ብር ወጪ የተገነባው የንጹህ መጠጥ ውኃ ፕሮጀክት ተመረቀ።

30

ባሕር ዳር: ግንቦት 04/2017 ዓ.ም (አሚኮ) በሰሜን ጎጃም ዞን የዱርቤቴ ከተማ አሥተዳደር በ2017 በጀት ዓመት የሠራቸውን መሠረተ ልማቶች አስመርቆ ለአገልግሎት ክፍት አድርጓል። የንጹህ መጠጥ ውኃ ፕሮጀክት፣ የኮሪደር ልማት፣ ሁለገብ ስታዲየም፣ የጌጠኛ ድንጋይ ንጣፍ የተመረቁት መሰረተ ልማቶች ናቸው።

በምረቃ ሥነ ሥርዓቱ የተገኙት የአማራ ክልል ውኃ ቢሮ ኀላፊ ማማሩ አያሌው (ዶ.ር) በዱርቤቴ ከተማ ለሌሎች ከተሞች አርዓያ የሚኾን መሰረተ ልማት ተገንብቶ በመጠናቀቁ የሚያስደስት ነው ብለዋል። የሕዝቡ የብዙ ጊዜ ጥያቄ የነበረው የንጹህ መጠጥ ውኃ ተጠቃሚነት በ185 ሚሊዮን ብር ወጪ መገንባቱንም ገልጸዋል።

በበርካታ ቦታዎች የንጹህ መጠጥ ውኃ መገንባቱን የተናገሩት ዶክተር ማማሩ የዱርቤቴን ልዩ የሚያደርገው መንግሥት እና ሕዝብ እጅና ጓንት ኾነው መሥራቱ ነው ብለዋል። ወጣቱ የሰላም እና የልማት ተሳታፊ እንዲኾን የተደረገው ጥረትም በተግባር መታየቱን ገልጸዋል። ባለፉት ሁለት ዓመታት ሰላም በመደፍረሱ የተደናቀፉ የልማት ሥራዎች መኖራቸውን ገልጸው በመከላከያ፣ በጸጥታ ኀይሉ እና በአመራሩ ትግል በአንድ በኩል ሰላምን የማስፈን፣ በሌላ በኩል ደግሞ ልማት መሠራቱን አንስተዋል። በቀጣይም ተጠናክሮ እንደሚቀጥል ገልጸዋል።

ሰላም የአንድ ጊዜ ብቻ ሳይኾን የየዕለት ሥራ ነው ያሉት ዶክተር ማማሩ ከአንድ ወገንም ስለማይመጣ ሁሉም በጋራ ጥረት የሚያሰፍነው መኾኑን ገልጸዋል። በአምራችነቱ እና እንግዳ ተቀባይነቱ የሚታወቀው የአካባቢው ማኅበረሰብ ያጋጠመውን የሰላም ችግር ተቋቁሞ በመሥራት ዛሬ ለደረሰበት ሰላም እና ልማት ደርሷል ብለዋል።

ዶክተር ማማሩ መሰረተ ልማቱ እንክብካቤ እና መስፋፋትን እንደሚፈልግ ገልጸው ኅብረተሰቡ በጥንቃቄ እንዲጠቀምበትም አሳስበዋል። የተመረቀው ፕሮጀክት የውኃ ችግር እንዳይኖር ተደርጎ መገንባቱን የገለጹት ዶክተር ማማሩ በቀጣይ ዓመትም ለንጹህ መጠጥ ውኃ አቅርቦቱ ተጨማሪ አንድ ጉድጓድ እንደሚቆፈር ቃል ገብተዋል።

የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous article”በጨለማ ውስጥ ብርሃን በሚታያቸው መሪዎች በሚሠሩ ሥራዎች ሀገር ይሻገራል” ድረስ ሳህሉ (ዶ.ር)
Next articleዘላቂ ሰላም እንዲሰፍን የበኩላቸውን እንደሚወጡ የማዕከላዊ ጎንደር ዞን ወጣቶች ተናገሩ።