
ባሕር ዳር: ግንቦት 04/2017 ዓ.ም (አሚኮ) በሰሜን ጎጃም ዞን የዱርቤቴ ከተማ አሥተዳደር በ2017 በጀት ዓመት የገነባቸውን የተለያዩ መሠረተ ልማቶች አስመርቆ ለአገልግሎት ክፍት አድርጓል። በምክትል ርእሰ መሥተዳድር ማዕረግ የገጠር ዘርፍ አስተባባሪ እና የግብርና ቢሮ ኀላፊ ድረስ ሣህሉ (ዶ.ር) ባለፉት ሁለት ዓመታት ክልሉ ያጋጠመው የሰላም እጦት ችግር ለልማት እንቅፋት ኾኖ መቆየቱን ገልጸዋል።
ዱርቤቴ እና የአካባቢዋ ሕዝብ ለችግሩ መፍትሄ በማበጀት ከመከላከያ ሠራዊት፣ ከክልሉ የጸጥታ ኃይል እና ከአመራሩ ጋር ተባብሮ የኮሪደር ልማትን በመፈጸሙ አመስግነዋል። “ሁልጊዜም በጨለማ ውስጥ ብርሃን በሚታያቸው መሪዎች በሚሠሩ ሥራዎች ሀገር ይሻገራል” ያሉት ዶክተር ድረስ ዱርቤቴ ከተማ ላይም ይህንኑ ዓይተናል ብለዋል። ችግር አለ ብለው ያልተቀመጡ አመራሮች ከሕዝባቸው ጋር በመተባበር ተጀምረው የነበሩ የንጹህ መጠጥ ውኃ ፕሮጀክቶ እና ሌሎች የልማት ሥራዎች ማጠናቀቃቸውን አንስተዋል።
ለአማራ ክልል የሚመጥነው እና የሚያምርበት የልማት ሥራዎችን ማፋጠን ነው። ባለፉት ዓመታት ሕዝቡ ያነሳቸው ከነበሩት ጥያቄዎች ውስጥ አንዱ እና ዋናው የመልማት ጥያቄ ነበር። እንዲህ ዓይነት ለሕዝብ ጠቃሚ ፕሮጀክቶችን በአጭር ጊዜ መፈጸም እና ማስመረቅ የክልላችን ቁልፍ አጀንዳ መኾን አለበት። ለዚህ ደግሞ ሰላም አስፈላጊ ነው ብለዋል።
የተጀመሩ እና ቃል የተገቡ የልማት ሥራዎች ተጠናቅቀው ሕዝብ እንዲጠቀም የሰላምን አስፈላጊነት ገልጸዋል። ሰላምን እና ልማትን በመውደድ እና በመተባበር ልማትን ስላረጋገጣችሁ እናመሰግናለን ብለዋል ዶክተር ድረስ ሳህሉ በመልዕክታቸው።
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!
