
ባሕር ዳር: ግንቦት 04/2017 ዓ.ም (አሚኮ) በአማራ ክልል ከመሪዎች ጋር በወቅታዊ የሰላም ጉዳዮች ዙሪያ ውይይት እየተደረገ ነው። በውይይቱ ርእሰ መሥተዳደር አረጋ ከበደ፣ የአማራ ክልል ብልጽግና ፓርቲ ቅርንጫፍ ጽሕፈት ቤት ኀላፊ ይርጋ ሲሳይን ጨምሮ ሌሎች ከፍተኛ የሥራ ኀላፊዎች ተገኝተዋል።
በውይይቱ ላይ መልዕክት ያስተላለፉት ርእሰ መሥተዳድር አረጋ ከበደ ሳይፈቱ እና ሳይስተካከሉ የቆዩ ችግሮች የክልሉን ሕዝብ ለፈተና ዳርገውታል ነው ያሉት። በተፈጠረው የጸጥታ ችግር ምክንያት ለዘመናት ያጠራቀምነው ሃብት፣ ያከማቸነው ወረት ተጎድቷል ብለዋል። የክልሉ ሕዝብም ሕይዎቱ እና ንብረቱ ለአደጋ ተጋልጦ መቆየቱን ነው የተናገሩት።
የክልሉ ሕዝብ በታሪኩ አይቶት በማያውቀው ችግር ውስጥ እያለፈ እንደሚገኝም አንስተዋል። ክልሉ ያለበት ችግር የሚያሳዝን እና ልብን የሚሰብር መኾኑንም ተናግረዋል። ፖለቲካን ከሰብዓዊነት በላይ መመልከት እንደማይገባም ገልጸዋል። ከሁሉም ሰብዓዊነት ይቀድማል ነው ያሉት። በክልሉ የተፈጠረው የጸጥታ ችግር ሰብዓዊ እና ቁሳዊ ጉዳት ማድረሱንም ተናግረዋል።
ግጭቱ ለማንም የማይጠቅም ነው ያሉት ርእሰ መሥተዳድሩ ክልሉ አስከፊ ጉዳት ቢደርስበትም ችግርን የመቋቋም አቅሙ የሚደንቅ ነው ብለዋል። ክልሉ በግጭት ውስጥ ኾኖ የልማት እና የመልካም አሥተዳደር ሥራዎችን እንደሚሠራም ተናግረዋል። የክልሉ ችግርን የመቋቋም ብቃት ብዙዎችን ያስገረመ መኾኑንም አንስተዋል። በችግር ውስጥ ኾነን ብዙ ሥራዎችን ሠርተናል ያሉት ርእሰ መሥተዳድሩ የሠራናቸው ሥራዎች ክልሉ በሰላማዊ እንቅስቃሴ ውስጥ ቢኾን ኖሮ ምን ልንሠራ እንደምንችል አመላካች ናቸው ብለዋል።
ክልሉ በችግርም ውስጥ ኾኖ መደበኛ ሥራውን የሚሠራ መኾኑንም አንስተዋል። በግጭት ውስጥ አገልግሎት እንሠጣለን፣ በግጭት ውስጥ እናመርታለን፣ በግጭት ውስጥ ገቢ እንሠበሥባለን፣ በግጭት ውስጥ መደበኛ አገልግሎት እንሰጣለን ብለዋል። ክልሉ ችግሮችን እንዲቋቋም የቀደሙ መሪዎች፣ አሁን ያሉ የሙያ መሪዎች እና ሕዝቡ ያደረጉት አስተዋጽኦ ከፍተኛ መኾኑን ገልጸዋል። ችግርን የመቋቋም ብቃትን አጠናክሮ መቀጠል እና ከቀደመው የተሻለ መሥራት እንደሚጠበቅም ተናግረዋል።
የሙያ መሪዎች የሕዝብን እርካታ ለማሳደግ፣ የሕዝብ እና የመንግሥትን ግንኙነት ለማጠናከር የሚኖራቸው አስተዋጽኦ ከፍተኛ መኾኑንም ገልጸዋል። የሙያ መሪዎች በሕዝብ እና በፖለቲካ መሪዎች መካከል ቁልፍ ሚና ያላቸው መኾናቸውን ተናግረዋል። ፍላጎትን ወደ ተግባር ለመቀየር ያላቸው አስተዋጽኦም የላቀ መኾኑን አንስተዋል። የመንግሥትን ፖሊሲ ወደ ዕቅድ እና ተግባር ለመቀየር የመሪዎች ሚና ከፍተኛ መኾኑን ገልጸዋል። በበጎ ምግባር አገልጋይ የኾነ ሠራተኛ በመገንባት ዜጎችን በፍትሐዊነት ለማገልገል የሚኖራቸው ሚናም ላቅ ያለ መኾኑን አንስተዋል።
ሠራተኞች በሙያዊ መርህ ላይ ተመስርተው ሕዝብን ማገልገል፣ ሥራዎችን በውጤታማነት እና በብቃት መሥራት፣ ችግሮች እንዲፈቱ አስተዋጽኦ ማድረግ ይጠበቃል ነው ያሉት። ግለሰባዊ ሥነ ምግባር እና ተቋማዊ እሴት በመላበስ ማገልገል እንደሚገባም አመላክተዋል። የአማራ ክልል ከፍተኛ የኾነ የመልማት ዕድል አለው ያሉት ርእሰ መሥተዳድሩ የመልማት ዕድሉን በውጤታማነት ለመጠቀም የሚያስችል ብቃት ያስፈልጋል ነው ያሉት። ጸጋን እና ተቋማዊ አቅምን በማቀናጀት ለኅብረተሰብ ዕድገት ሥራ መሥራት ይገባል ነው ያሉት።
ከግጭት እና ከድኅነት አዙሪት መውጣት እንደሚገባም ተናግረዋል። የግጭት አዙሪት ከልብ በመጸጸት መውጣት እንደሚገባውም ገልጸዋል። ዕድሎችን በላቀ ደረጃ በመጠቀም ክልሉን አሁን ካለበት ያልተገባ አውድ ማውጣት ይገባልም ነው ያሉት።
ክልሉን ከችግር ለማውጣት የመሪዎች ሚና ከፍተኛ መኾኑንም ተናግረዋል። ሕዝብን በቀናነት እና በትጋት ማገልገል እንደሚገባም ገልጸዋል። በክልሉ የሰላም እና የልማት ጉዳዮች መክረው አቅጣጫ እንደሚያስቀምጡም ተናግረዋል።
ሕዝብን ያጎሳቆሉ ችግሮችን በመለየት መፍትሔ ማስቀመጥ አለብን ነው ያሉት። የዜጎቻችን የዓላማ አገልጋዮች መኾን አለብን ብለዋል። ለዓላማ እና ለምናገለግለው ሕዝብ ተግተን መሥራት አለብን ነው ያሉት። በገጠሙን ችግሮች እና ቀጣይ በሚኖሩ ጉዳዮች ዙሪያ መወያየት እንደሚጠበቅም አንስተዋል።
ዘጋቢ፦ ታርቆ ክንዴ
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን