“የሕዝብ ጥያቄዎች እንዲፈቱ መሪዎች የማይተካ ሚና አላቸው” አቶ ይርጋ ሲሳይ

40

ባሕር ዳር: ግንቦት 04/2017 ዓ.ም (አሚኮ) በአማራ ክልል ከመሪዎች ጋር በወቅታዊ የሰላም ጉዳዮች ዙሪያ ውይይት እየተደረገ ነው። በውይይቱ ርእሰ መሥተዳደር አረጋ ከበደ፣ የአማራ ክልል ብልጽግና ፓርቲ ቅርንጫፍ ጽሕፈት ቤት ኀላፊ ይርጋ ሲሳይን ጨምሮ ሌሎች ከፍተኛ የሥራ ኀላፊዎች ተገኝተዋል።

በውይይቱ ላይ መልዕክት ያስተላለፉት የአማራ ክልል ብልጽግና ፓርቲ ቅርንጫፍ ጽሕፈት ቤት ኀላፊ ይርጋ ሲሳይ የአማራ ክልል በውሥብሥብ ችግር ውስጥ መቆየቱን ተናግረዋል። በብዙ መስዋዕትነት አንጻራዊ ሰላም መፈጠሩንም ገልጸዋል። የሰላም ችግሮችን ከመፍታት ጎን ለጎን የልማት ሥራዎችም እየተሠሩ መኾናቸውን ነው የተናገሩት። ባለፉት ዓመታት የአማራ ክልል ሕዝብ መጠቀም የሚገባውን ሳይጠቀም በመቆየቱ ታግሎ ለውጥ ማምጣቱን አስታውሰዋል።

በመጣው ለውጥ መጠቀም ሲገባው ግን ያልተገባ ትርክት በመሠራቱ ለችግር ተዳርጎ ቆይቷል ነው ያሉት። ለውጡ ብዙ መስዋዕትነት ተከፍሎ የመጣ ነው ያሉት ኀላፊው ከለውጡ ማግስት የአማራ ክልል ሕዝብ መጠቀም ሲገባው በተሠራው ያልተገባ ሥራ ለችግር ተዳርጎ ቆይቷል ብለዋል።

የክልሉን ሕዝብ ከችግር ለማውጣት እየተሠራ መኾኑንም አንስተዋል። የልማት ሥራዎችን ለማስቀጠል፣ የክልሉን ፖለቲካ ለማረጋጋት በተሠሩ ሥራዎች ውጤቶች መገኘታቸውን ገልጸዋል። የአማራ ክልል ሕዝብ አስተማማኝ ሰላም ይፈልጋል ያሉት ኀላፊው ከዚህ በላይ ልማት፣ ለውጥ እና ዕድገት ይፈልጋል ነው ያሉት።

የአማራ ክልል ሕዝብ ጥያቄዎቹ በሰላማዊ መንገድ እንዲፈቱለት እንደሚፈልግም ገልጸዋል። “የሕዝብ ጥያቄዎች እንዲፈቱ ደግሞ መሪዎች የማይተካ ሚና አላቸው” ብለዋል። መሪዎች አንድ ኾነው እና ተደጋግፈው፣ የሕዝብን መብት እና ጥቅም ማስከበር አለባቸው ነው ያሉት። መሪዎች የሕዝብን ጥቅም ማስከበር አለብን ብለው በቁርጠኝነት ሲነሱ ብዙ ነገር ይቀየራል ብለዋል።

መሪዎች አንድነታቸውን ሲያጠናክሩ በጋራ ጉዳይ በጋራ መግባባት ሲችሉ ጥያቄዎችን መፍታት፣ አለመረጋጋትን መቅረፍ እና ዕድገትን ማረጋገጥ ይቻላል ነው ያሉት። በክልሉ ተደጋጋሚ ውይይቶች መደረጋቸውንም ገልጸዋል። በተደረገው ውይይትም ለውጥ ታይቷል ነው ያሉት።

የጽንፈኝነት አስተሳሰብን ማስተካከል ካልቻልን በስተቀር የአማራን ሕዝብ ስቃይ እናራዝመዋለን ብለዋል። በቁርጠኝነት ጽንፈኝነትን መታገል እና በቃህ ማለት እንደሚገባ አመላክተዋል። የውስጥ እና የውጭ ጫናዎችን መቋቋም የሚችል ቁመና ላይ መድረስ እንደሚገባም አንስተዋል።

በክልሉ በተፈጠረው የጸጥታ ችግር ምክንያት በርካታ ወገኖች ላይ ጉዳት መደረሱንም ተናግረዋል። መሪዎች የተገኘውን አንጻራዊ ሰላም ዘላቂ ለማድረግ እና ችግሮችን ለመፍታት ብዙ ይጠበቅባቸዋል ነው ያሉት።

ዘጋቢ፦ ታርቆ ክንዴ

የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን

Previous articleየደም ካንሰር እና ሕክምናው!
Next article“ዕድሎችን በላቀ ደረጃ በመጠቀም ክልሉን አሁን ካለበት ያልተገባ አውድ ማውጣት ይገባል” ርእሰ መሥተዳድር አረጋ ከበደ