1 ነጥብ 75 ቢሊዮን ችግኝ ለመትከል ዝግጅት መደረጉን የአማራ ክልል ግብርና ቢሮ አስታወቀ፡፡

727

ችግኞችን ከመትከል ባሻገር መንከባከብ እና ማፅደቅ፣ ነባር ደኖችንም መጠበቅ እንደሚገባ የዘርፉ ተመራማሪ ጠቁመዋል፡፡

የደን ሽፋኑን ለማሳደግ በኢትዮጵያ በየዓመቱ በቢሊዮን የሚቆጠሩ ችግኞች ይተከላሉ፡፡ አማራ ክልልም በየዓመቱ በሥፋት የችግኝ ተከላ ከሚካሄድባቸው የሀገሪቱ አካባቢዎች ይጠቀሳል፡፡ በያዝነው ዓመትም 1 ነጥብ 75 ቢሊዮን ችግኝ በ187 ሺህ 492 ሄክታር መሬት ላይ ለመትከል ዝግጅት እየተደረገ እንደሚገኝ ከአማራ ክልል ግብርና ቢሮ ያገኘነው መረጃ ያሳያል፡፡ ለተከላ ከተዘጋጁት መካከል 82 ሺህ 864 ያህሉ ለጥምር ደን ልማት የሚውል ናቸው፡፡ ቀሪው ደግሞ ለደን አገልግሎት እንደሚሆን የአማራ ክልል ግብርና ቢሮ የሕዝብ ግንኙነት ባለሙያ አቶ አንተነህ ሰውአገኝ ለአብመድ ገልጸዋል፡፡

ለመሆኑ የነበረውን የደን ብዝኃ ሕይወት ለመመለስ እየተደረገ ያለው ጥረት እንዴት ይታያል? አብመድ ከደንና ብዝኃ ሕይወት ተመራማሪና የአመልድ ዋና ዳይሬክተር ዓለማየሁ ዋሴ (ዶክተር) ጋር ቆይታ አድርጓል፡፡ እንደ ዶክተር ዓለማየሁ ማብራሪያ ደንና የውኃ አካላት የብዝኃ ሕይወት መገኛ ናቸው፡፡ ከመሬት በላይ ያሉ በራሪ፣ ተሳቢና ተራማጅ እንስሳት እንዲሁም በመሬት ውስጥ ያሉ በዐይን የማይታዩ ፍጡራን የመኖር ኅልውና የተመሠረተውም በብዝኃ ሕይወት ደኅንነት ላይ ነው፡፡ ይህንን ለመጠበቅ በመንግሥት በኩል ያለው ፍላጎትና ተነሳሽነት መልካም እንደሆነ ዶክተር ዓለማየሁ ተናግረዋል፡፡ እየባከነ ባለው ጉልበትና ገንዘብ ልክ ግን ውጤት እየመጣ አለመሆኑን ነው ያስረዱት፡፡ እንደ ተመራማሪው ማብራሪያ የችግሩ ዋነኛ መንስኤ ደግሞ የደን ሽፋኑን በተመለከተ በትክክል የተቀመጠ ግብ አለመኖሩ ነው፡፡ ‘‘ገንዘብ ወጥቶባቸው በየዓመቱ የሚፈሉ ችግኞችን ማን? እንዴት ባለ መሬት? ለምን ዓላማ ይተክላቸዋል? እንዴትስ ይንከባከባቸዋል? የሚለውን መለየት ላይም ችግር መኖሩን ጠቁመዋል፡፡

እንደ ዶክተር ዓለማየሁ ማብራሪያ የደን ብዝኃ ሕይወት የተለያዩ ዝርያ ያላቸውን ዕፅዋት በመትከል፣ በመንከባከብና በማልማት የሚመጣ ነው፡፡ ለዚህ ደግሞ የተፈጥሮ ደንን መጠበቅ ያስፈልጋል፡፡ ይህ ባለመሆኑ ግን ከዓመታት በፊት በጥቅጥቅ ደን ተሸፍነው የነበሩ ቦታዎች ተራቁተዋል፡፡ በኢኮኖሚያዊ ጠቀሜታውም፣ በካርቦን ይዘቱም ከአንድ ችግኝ አንድ ዛፍ እንደሚበልጥ በመገንዘብ፣ ችግኖች ዛፍ እንሰሚሆኑ የሚወስደው ጊዜም ረዥም በመሆኑ፣ ችግኝ ከመትከል ጎን ለጎን የቆዩ ዛፎችን መንከባከብ እንደሚገባ ተመራማሪው መክረዋል፡፡ በዚህም የተጋረጠውን የተፈጥሮ ሀብት መመናመን በአዲስ የደን ልማት አማካኝነት ማካካስ እንደሚቻል ነው ያስገነዘቡት፡፡ አዲስ የደን ልማት የሚካሄደው ያወደምነውን ዛፍ ለመተካትና ወደፊት የሚመጣው ትውልድ የመጠቀም ዕድል እንዲኖረው ታሳቢ በማድረግ መሆን እንዳለበትም አመላክተዋል፡፡ ከኢኮኖሚያዊ፣ ከብዝኃ ሕይወታዊ ጥበቃና ከሥነ-ውበት ጠቀሜታቸው አንፃር ማየትና የሚተከሉበትን ቦታ ቀድሞ መለየትም ከአስፈላጊ ተግባራት መካከል ናቸው፡፡ የተዘጋጁ ችግኞች እንደ የባሕሪያቸው ሊተክሉና ሊንከባከቡ የሚችሉ ማኅበረሰብ ክፍሎችን በመለየት ወደ ሥራ መግባት ከተቻለ ካለፉት ጊዜያት በተሻለ ውጤታማ የደን ልማት ማልማት እንደሚቻል ዶክተር ዓለማየሁ መክረዋል፡፡

የአማራ ክልል ግብርና ቢሮ የሕዝብ ግንኙነት ባለሙያው አቶ አንተነህ ሰው አገኝ በቀረቡት ምክረ ሀሳቦች ላይ አስተያየት ሰጥተዋል፡፡
እንደ አቶ አንተነህ ሀሳብ ኅብረተሰቡ በጋራ ወጥቶ ችግኞችን መትከሉ ግንዛቤውን ለማሳደግ የሚረዳ ቢሆንም የተከላ እና የእንክብካቤ ሂደቱን ሳይንሳዊ መንገድን የተከተለ በማድረግ በኩል ችግሮች ይስተዋላሉ፡፡ ባለፈው ዓመት በአንድ ቀን በተካሄደው የችግኝ መትከል መርሃ ግብር ከተሳተፉ ተቋማትና ግለሰቦችም የተከሏቸው ችግኞች እንዲጸድቁ እየተንከባከቡ ያሉት ውስን መሆናቸውንም አሳውቀዋል፡፡ ከችግኞች ቀጥተኛ ተጠቃሚ የሆነው ማኅበረሰብ የሚተክላቸው ላይ የተሻለ የጽድቀት መጠን ስለሚስተዋል ይህን ማበረታታ የተሻለ ሊሆን እንደሚችልም ነው ያመላከቱት፡፡

በቀጣይ የክረምት ወራት ተቋማት የሚተክሏቸውን ችግኞች ተንከባክበው እንዲያሳድጉ ርክክብ በመፈፀም ችግሮችን ቀደም ብሎ ለማስተካከል እንደሚያስፈልግ ታምኖ ግብርና ቢሮው እየሠራ እንደሚገኝም የሕዝብ ግንኙነት ባለሙያው ተናግረዋል፡፡

በ2011/2012 የክረምት ወቅት 1 ነጥብ 57 ቢሊዮን ችግኞች ተተክለዋል፡፡ ችግኞቹ የተተከሉት በ295 ሺህ 350 ሄክታር መሬት ላይ ነው፡፡ በ88ሺህ 451 ሄክታር መሬት ላይ ለደን ዛፍ የተተከሉ ናቸው ብሏል ግብርና ቢሮው፡፡ 86 ሺህ 218 ሄክታር መሬት ደግሞ በጥምር ደን ችግኞች ነው የተሸፈነው፡፡ ቀሪው ሄክታር መሬት በስነ ህይዎታዊ ዘዴ የተሸፈነ መሆኑን ነው ቢሮው ያሳወቀው፡፡ እንደ ቢሮው መረጃ ባለፈው ጥቅምትና ህዳር በተደረገው የአንደኛው ዙር የዳሰሳ ጥናት በዓመቱ ከተተከለው ችግኝ ውስጥ 84 በመቶው ፀድቋል፡፡ በያዝነው 2012/2013 ክረምት ወቅት የተከላ ዘመን ደግሞ 1 ነጥብ 75 ቢሊዮን ችግኝ ለመትከል ታቅዷል፤ በዚህም 187ሺህ 492 ሄክታር መሬት በችግኝ ይሸፈናል፡፡

ዘጋቢ፡- ኃይሉ ማሞ

Previous article“ኢትዮጵያ በዓባይ ውኃ አጠቃቀም ላይ እስካሁን ድረሰ ጥቅሟን የሚያስነካ ውል አልፈረመችም፤ ወደፊትም አትፈርምም፤ መፈረምም የለባትም፡፡” ዶክተር ይልማ ስለሺ
Next articleበኮሮና ቫይረስ የተያዙ ሰዎች ቁጥር ከአምስት ሚሊዮን አለፈ፡፡