
ደብረ ታቦር: ግንቦት 04/2017 ዓ.ም (አሚኮ) በደቡብ ጎንደር ዞን ሊቦ ከምከም ወረዳ በይፋግ ክላስተር ሥር የሚገኙ የሰባት ቀበሌ ነዋሪዎች የክልል፣ የዞን እና የወረዳ የሥራ ኀላፊዎች በተገኙበት በሰላም ዙሪያ ውይይት አድርገዋል። በሊቦ ከምከም ወረዳ የውሻ ጥርስ ቀበሌ እና አካባቢው የኦርቶዶክስ እና የእስልምና ሃይማኖት ከተታዮች ለረጅም ጊዜ ክፉና ደጉን በጋራ ያሳለፉ ሕዝቦች ናቸው።
ይኹን እንጅ በአካባቢው የተከሰተውን የጸጥታ ችግር እንደ ጥሩ አጋጣሚ በመጠቀም የፖለቲካ ትርፍ ለማግኘት ያሰቡ ውስን ቡድኖች በሁለቱ በጋራ በኖሩ ሕዝቦች መከላከል መጠራጠር እንዲፈጠር ማድረጋቸውን የውይይቱ ተሳታፊ አባቶች ገልጸዋል። በነዋሪዎች መካከል ልዩነት መፍጠር ተገቢ አለመኾኑን በመረዳት በሃይማኖቱ አባቶች እና በሀገር ሽማግሌዎች ሲሠራ መቆየቱንም ገልጸዋል።
በሁለቱ የሃይማኖት ተከታዮች መካከል ልዩነት ለመፍጠር ሢሠሩ የነበሩ ግለሰቦች በሕግ ስር እንዲኾኑም ተጠይቋል ነው ያሉት። በቀጣይም አካባቢያቸውን በጋራ እንደሚጠብቁ ተናግረዋል። በውይይቱ ላይ የተገኙት የኦርቶዶክስ ሃይማኖት ተከታይ አባት እንደተናገሩት “ማንኛውም የእምነት ሰው የሰላም እንጅ የችግር ምክንያት ሊኾን እንደማይገባ” መክረዋል።
ልዩነትን፣ ጠብን እና ጥላቻን በማስወገድ ሃይማኖታዊ አስተምህሮው የሚያዘውን ሰዎችን ማክበር፣ የአብሮነት እና የመደጋገፍ ግብረ ገብነትን ማጠናከር ይገባል ነው ያሉት። ሃይማኖታዊ አስተምህሮው የማይፈቅደውን ሥርቆት እና ጥላቻን ደግሞ ማውገዝ እንደሚገባም መክረዋል። ከዚህ በፊት ችግር የፈጠሩ ሰዎችም እንዲታረሙ የመንግሥት ኀላፊነት ሊኾን ይገባል ብለዋል።
የእስልምና ሃይማኖት ተከታይ አባት እንዳሉት ደግሞ እስልምና ሰላም፣ መቻቻል በመኾኑ የሚነሱ ችግሮችን በሰላማዊ መንገድ መፍታት ይገባል ብለዋል። ተቻችለው በጋራ የኖሩ የሃይማኖቱ ተከታዮችን በማጋጨት የራስን ፍላጎት ለማሟላት የሚሠሩ ግለሰቦችን ማጋለጥ እንደሚገባም አንስተዋል። ለዚህ ደግሞ በየጊዜው በመገናኘት መወያየት እና ችግር ፈጣሪዎችን መምከር ይገባል ነው ያሉት።
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን