
ባሕር ዳር : ግንቦት 02/2017 ዓ.ም (አሚኮ) የባሕር ዳር ከተማ አሥተዳደር ከፍተኛ የሥራ ኀላፊዎች የከተማዋን የምሽት የኮሪደር ልማት ሥራዎች ተዘዋውረው ጎብኝተዋል። የመጀመሪያው ዙር የኮሪደር ልማት የኤሌክትሪክ መብራት ዝርጋታም ተጠናቅቋል።
ተፈጥሮን እና ፀጋዎቿን ድር እና ማግ ያደረገላት የኮሪደር ልማት የመጀመሪያው ዙር ተጠናቅቆ ሁለተኛው ዙር ከተጀመረ ቀናት ተቆጥረዋል።
የኮሪደር ልማት ሥራዎች በባሕር ዳር ከተማ ከሌሎች አካባቢዎች ይለያል ያሉት የከተማ አሥተዳደሩ ተቀዳሚ ምክትል ከንቲባ ጎሹ እንዳላማው የከተማዋ የኮሪደር ልማት ሥራዎች የጣና ሐይቅ ዳርቻ ልማት ሥራዎችንም ያጠቃልላል ብለዋል።
የኮሪደር ልማት ሥራው የከተማውን ተፈጥሯዊ ፀጋ የገለጠ መኾኑ የከተማውን ሕዝብ ድጋፍ እና እገዛ እንድናገኝ እረድቶናል ነው ያሉት። ይህም የመጀመሪያውን ዙር አገባድደን ሁለተኛውን ዙር እንድንጀምር ጉልበት ኾኖናል ብለዋል።
የመጀመሪያው ዙር የኮሪደር ልማት ሥራዎች የኤሌክትሪክ መብራት ሥራዎች ተጠናቅቆ አገልግሎት መስጠት ጀምሯል።
የባሕር ዳር ከተማ የመጀመሪያ ዙር የኮሪደር ልማት የመብራት ሥራ ተጠናቅቋል ያሉት ተቀዳሚ ምክትል ከንቲባው ጥቃቅን ቀሪ ሥራዎችን በቅርብ እንጨርሳለን ነው ያሉት።
የከተማዋን ውበት እና የነዋሪዎችን ደስታ የገለጡ የኮሪደር ልማት ሥራዎችን ቀን ከሌሊት ለሠሩ እና ላስተባበሩ ሁሉ ምሥጋና አቅርበዋል። “ጀምረን ጨርሰናል፤ ሕዝብን ማገልገል መታደል መኾኑን ስላየን አሁንም እንደገና ጀምረናል፤ ይህንን አጠናቅቀን በድጋሜ እንገናኛለን” ብለዋል።
የኤሌክትሪክ ተሽከርካራዎች ቻርጅ ማድረጊያ ቦታዎችም በከንቲባው እና በከፍተኛ መሪዎቹ ተጎብኝተዋል።
ዘጋቢ፦ ታዘብ አራጋው
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን