የአማራን ሕዝብ ለማጎሳቆል የተነሱ የውስጥ እና የውጭ ጠላቶችን አምርሮ መታገል ይገባል።

31

ባሕር ዳር: ግንቦት 02/2017 ዓ.ም (አሚኮ) የዞን፣ የክልል እና የሀገር መከላከያ ሠራዊት የሥራ ኀላፊዎች በተገኙበት በደቡብ ጎንደር ዞን ከአዲስ ዘመን ከተማ አሥተዳደር የጸጥታ መዋቅር ጋር ውይይት ተደርጓል።

የአማራ ክልል ሰላም እና ጸጥታ ቢሮ ምክትል ኀላፊ በሪሁን መንግሥቴ እንዳሉት ባለፉት ሁለት ዓመታት በክልሉ ሕዝብ ላይ የደረሰው ጉዳት በውጭ ጠላት እንኳ ይፈጸማል ተብሎ የማይታሰብ ነው።

በተለይም ደግሞ የክልሉን ሕዝብ ሰላም እና ደኅንነት የሚያስጠብቁ የጸጥታ አባላት ቤተሰቦችን ጭምር በማፈን የአማራን ሕዝብ ሥነ ልቦና በማይመጥን መንገድ የጭካኔ ርምጃ እንደተወሰደባቸው ገልጸዋል።

የሀገር መከታ እና የአፍሪካ ኩራት የኾነውን የሀገር መከላከያ ሠራዊት እንደጠላት እንዲቆጠር የተሠራው ሥራ መከሸፉንም ገልጸዋል።

“ለአማራ ሕዝብ እታገላለሁ” የሚለው ቡድን ዳግም የአማራን ሕዝብ ለማስጨፍጨፍ በጠላትነት ፈርጀው ላለፉት አስርት ዓመታት ሲጨፈጭፉ እና ሲያስጨፈጭፉ ከነበሩ የውስጥ እና የውጭ ኀይሎች ጋር እየሠራ መኾኑንም ገልጸዋል።

እነዚህን ሀገርን ለማፍረስ የተነሱ ኀይሎችን መመከት እና ማሳፈር የሚቻለው ውስጣዊ አንድነትን በማጠናከር በጽናት መታገል ሲቻል መኾኑንም ገልጸዋል።

በቀጣይ የሰላም አማራጭን በማይከተሉ ኀይሎች ላይ ከሌሎች የጸጥታ መዋቅር ጋር በመቀናጀት የሕግ ማስከበር ሥራው ተጠናክሮ ይቀጥላል ብለዋል።

በውይይቱ የተገኙት የሀገር መከላከያ ሠራዊት ተወካይ ሰላምን በማይከተሉ ቡድኖች ላይ ርምጃው ተጠናክሮ እንደሚቀጥል ገልጸዋል።

ማኅበረሰቡም ከሠራዊቱ ጎን በመቆም ማኅበረሰቡን የሚዘርፉ ቡድኖችን እንዲታገል አሳስበዋል።

የደቡብ ጎንደር ዞን ሚሊሻ መምሪያ ኀላፊ በላይ አያሌው የዞኑ የጸጥታ መዋቅር ከማኅበረሰቡ ጋር በመቀናጀት በወሰደው ርምጃ የማኅበረሰቡን ደኅንነት የማረጋገጥ ሥራ ተሠርቷል ብለዋል።

በቀጣይ ውስጣዊ አቅምን የበለጠ በማጠናከር የሰላም አማራጭን በማይከተሉ ቡድኖች ላይ የተጠናከረ እርምጃ ይወሰዳል ብለዋል።

የአዲስ ዘመን ከተማ አሥተዳደር ከንቲባ አዱኛ ጥጋቡ ለአካባቢው የጸጥታ አባላት የሚገባውን የመኖሪያ ቦታ እና ከጤና ጋር ለተነሱ ጥያቄዎች ሕጋዊ አሠራሩን በተከተለ መንገድ ለመፍታት የቅደመ ዝጎጅት ሥራ እየተሠራ መኾኑንም ገልጸዋል።

የአማራ ሕዝብ በራሱ ልጆች ከስብዕና ውጭ የኾነ ድርጊት እንደተፈጸመበት በጸጥታ አባላት ተነስቷል። ችግሩን ለመቅረፍ ከሀገር መከላከያ ሠራዊት ጋር በመቀናጀት አኹን ለደረሰው ሰላም ማድረሳቸውን ገልጸዋል።

በቀጣይ ለክልሉ የጸጥታ መዋቅር በተለይም ደግሞ በየአካባቢው ለተደራጀው የጸጥታ አባላት የተደራጀ ድጋፍ ከተደረገ ክልሉን ወደ መደበኛ ሰላሙ መመለስ የሚያስች አቅም እንዳለ ነው የተናገሩት።

ዘጋቢ፦ ዳግማዊ ተሠራ

የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን

Previous article“የሃይማኖት አባቶች እና የሀገር ሽማግሌዎች ለሕዝብ ብለው ዕውነትን መድፈር አለባቸው” መንገሻ ፈንታው (ዶ.ር)
Next articleየፌደራል የመንግሥት የሥራ ኀላፊዎች በዘጠንኛው የመላ አማራ ጨዋታ ለመታደም ኮምቦልቻ ገቡ።