
ባሕር ዳር: ግንቦት 02/2017 ዓ.ም (አሚኮ) የባሕር ዳር ከተማ አሥተዳደር “የጥፋት እጆች እና መዘዞቹ” በሚል መሪ መልዕክት ከሃይማኖት አባቶች እና ከሀገር ሽማግሌዎች ጋር ሰላምን ማጽናት ዓላማው ያደረገ የምክክር መድረክ በባሕር ዳር ከተማ እያካሄዱ ነው።
በውይይቱ ላይ የተገኙ የሃይማኖት አባቶች እና የሀገር ሽማግሌዎች ዘላቂ ሰላም ይመጣ ዘንድ አጥብቀው እንደሚሹ ገልጸዋል።
በውይይት መድረኩ የተገኙት የአማራ ክልል የመንግሥት ኮሙዩኒኬሽን ቢሮ ኀላፊ መንገሻ ፈንታው (ዶ.ር) በክልሉ የተለያዩ ከተሞች ላይ የሃይማኖት አባቶች እና የሀገር ሽማግሌዎች በሀገራቸው የሰላም ሁኔታን አስመልክተው ውይይት እያደረጉ ነው ብለዋል።
አሁን ላይ ያለንበትን መሠረታዊ የኾነ የጸጥታ ችግር ለመቅረፍ የሃይማኖት አባቶች እና የሀገር ሽማግሌዎች ሚና ከፍተኛ እንደኾነ ገልጸዋል።
የሃይማኖት አባቶች እና የሀገር ሽማግሌዎች መንግሥት ከዚህ በፊት ያደረጋቸውን ሕዝባዊ ውይይቶች እና እየወሰደው ያለውን የሰላም አማራጭ በተለያዩ መድረኮች እያመሠገኑ እንደኾነም ተናግረዋል።
የአማራ ሕዝብ ከዚህ በላይ በሰላም እጦት ውስጥ መቀጠል እንደሌለበት መንገሻ ፈንታው (ዶ.ር) በአጽንኦት ተናግረዋል። ለዚህ ደግሞ መንግሥት በቁርጠኝነት መሥራቱን ይቀጥላል ነው ያሉት።
ዛሬም ኾነ ነገ ልክ እንደ ትናንቱ መንግሥት ለሰላም በሩን ክፍት እንዳደረገ ይቀጥላል ብለዋል። ነገር ግን በዘገየ ቁጥር የሕዝቡ እንግልት እየከፋ በመኾኑ ሰላምን በማይመርጡ ላይ ሕግ የማስከበር ርምጃው ተጠናክሮ ይቀጥላል ነው ያሉት።
በአጭር ጊዜ ውስጥ የክልሉ የሰላም ጉዳይ መልክ ይይዛል ብለን እናስባለን ብለዋል። “የሃይማኖት አባቶች እና የሀገር ሽማግሌዎች ስለ ሕዝብ ብለው ለዕውነት መድፈር አለባቸው” ነው ያሉት።
የሀገር ሽማግሌዎችን፣ የሃይማኖት አባቶችን እና ለትውልድ የቆሙ መምህራንን ማንገላታት መቆም አለበት ብለዋል። ለዚህ ደግሞ ሁሉም ሊያገባው ይገባል ነው ያሉት።
የጽንፈኛ ኀይሎች እንኳ ጥቅም የሚያገኙት ሰላም ሲኖር ነው ያሉት ቢሮ ኀላፊው አሁን ላይ እርስ በእርሳቸው እየተፋጁ እንደኾነ ነው የተናገሩት።
በክልሉ የተጀመሩ ልማቶች እንዲጠናቀቁ እና አዳዲስ ልማቶች እንዲጀመሩ ሰላም መፈጠር አለበት ብለዋል። የሰላም እጦቱን እንደ ጥሩ አጋጣሚ በመጠቀም ብልሹ አሠራር ላይ የተሰማሩ አካላትን ማጋለጥ እንደሚገባም መንገሻ ፈንታው (ዶ.ር) ተናግረዋል።
ዘጋቢ: ሰለሞን አንዳርጌ
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን