
አዲስ አበባ: ግንቦት 02/2017 ዓ.ም (አሚኮ) የሥራና ክህሎት ሚኒስቴር ከሚያዝያ 27 እስከ ግንቦት 2 ሲካሄድ የነበረው አራተኛው የኢትዮ ክህሎት ዉድድር ማጠቃለያ ተካሂዷል።
“ብሩህ አእምሮዎች በክህሎት የበቁ ዜጎች” በሚል መሪ መልዕክት በተካሄደው አራተኛው የኢትዮ ክህሎት ዉድድር ማጠቃለያ በምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ማዕረግ የዲሞክራሲ ሥርዓት ግንባታ ማዕከል ኀላፊ እና የብልጽግና ፓርቲ ምክትል ፕሬዝዳንት አደም ፋራህ፣ የሥራና ክህሎት ሚኒስትሯ ሙፈሪያት ካሚልን ጨምሮ ሌሎች ሚኒስትሮች እና ባለድርሻ አካላት ተገኝተዋል።
በማጠቃለያ ዝግጅቱ በምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ማዕረግ የዴሞክራሲ ሥርዓት ግንባታ ማዕከል ኀላፊ እና የብልጽግና ፓርቲ ምክትል ፕሬዝዳንት አደም ፋራህ እንደዚህ አይነት ዉድድሮች መነሳሳትን በመፍጠር ቴክኖሎጂዎችን ለማልማት እና ለማሻሻል ሚናቸው የላቀ ነው ብለዋል።
በውድድሩ የተሳተፉ እና ያሸነፉት ያሳዩት ብቃት፣ ክህሎት እና እውቀት የሚደነቅ መኾኑን ተናግረዋል። ለሀገሪቱ ችግሮች ተጨባጭ መፍትሄዎችን በመስጠት ተኪ ምርቶችን የሚያመርቱ ቴክኖሎጂዎችን በማፍለቅ የወደፊት ተስፋ ናችው ብለዋቸዋል ተወዳዳሪዎችን።
የኢትዮጵያ ብልጽግና አይቀሬ መኾኑ ማሳያ ናችሁ፣ ለጥረታችሁ እና ላሳያችሁት ቁርጠኝነት እንኳን ደስ አላችሁ ሲሉም ተናግረዋል። መንግሥትም የሚጠበቅበትን ድጋፍ ያደርጋል ብለዋል።
የሥራና ክህሎት ሚኒስትሯ ሙፈሪያት ካሚል ውድድሩ የተሻሉ ኢንተርፕራይዞችን እና ቴክኖሎጂዎችን ያየንበት፣ ችግር ፈቺ የምርምር ዉጤቶችን ያገኘንበት እንዲኹም እርስ በእርስ መማማር የተፈጠረበት ነው ብለዋል።
በሀገሪቱ በሚገኙ ቴክኒክና ሙያ ኮሌጆች መንግሥት እየተገበራቸው ያሉ ማሻሻዎች ተጨባጭ ዉጤቶችን እያመጡ መኾኑን የተመለከትንበት ነው ሲሉ ገልጸዋል።
በአራተኛው ሀገር አቀፍ ውድድር አንደኛ ለወጡ ግማሽ ሚሊዮን፣ ሁለተኛ ለወጡ 4 መቶ ሺህ ብር፣ ሦስተኛ ለወጡት ደግሞ 3 መቶ ሺህ ብር እና ሌሎች ሽልማቶች ተሰጥተዋል።
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን