“እንደ ሕዝብ ከልብ በመነጨ ኀላፊነት መነጋገር እና ማሰብ ይጠበቅብናል” ተቀዳሚ ምክትል ከንቲባ ጎሹ እንዳላማው

17

ለሰላም ሲባል ከመጸለይ ባሻገር ብዙ ርቀቶችን መሄድ እንደሚያስፈልግ የባሕር ዳር ከተማ የሃይማኖት አባቶች እና የሀገር ሽማግሌዎች ተናገሩ።

ባሕር ዳር: ግንቦት 02/2017 ዓ.ም (አሚኮ) የባሕር ዳር ከተማ አሥተዳደር “የጥፍት እጆችና መዘዞቹ” በሚል መሪ መልዕክት ከሃይማኖት አባቶች እና ከሀገር ሽማግሌዎች ጋር ሰላምን ማጽናት ዓላማው ያደረገ የምክክር መድረክ በባሕር ዳር ከተማ እያካሄደ ነው።

በውይይቱ ላይ የተገኙ የሃይማኖት አባቶች እና የሀገር ሽማግሌዎች ዘላቂ ሰላም ይመጣ ዘንድ አጥብቀው እንደሚሹ ገልጸዋል።

የባሕር ዳር ሀገረ ስብከት ዋና ጸሐፊ መልዓከ ብርሃን ፍስሐ ጥላሁን ሰላም ለሰው ልጅ ብቻ ሳይኾን በምድር ላይ ላሉ ፍጥረታት ሁሉ መሠረታዊ ነገር ነው ብለዋል።

ይሁንና ሰላምን የሚያጠፋውም ኾነ የሚያለማው የሰው ልጅ በመኾኑ ሰዎች ለሰላም ዋጋ ልንሰጥ ይገባል ነው ያሉት። ሁላችንም የሃይማኖት አባቶች በቁርጠኝነት ሰላምን መስበክ እና አባታዊ ኀላፊነታችንን መወጣት አለብን ብለዋል። ስለ ሰላም ከመጸለይ ባሻገርም ብዙ ርቀቶችን መሄድ ይጠበቅብናል ነው ያሉት።

የአማራ ክልል ሽምግልና ሥርዓት ማኅበር ሥራ አሥፈጻሚ ሼህ ከድር ያሲን አደም በአማራ ክልል ያለው የጸጥታ ችግር ወደ ሰላም እንዲመጣ እንደ ማኅበር ጥረቶችን እያደረጉ እንደኾነ ተናግረዋል።

ጦርነት ጥፋት እንጂ በረከት የለውም ያሉት ሼህ ከድር ድሮ የነበረው አብሮነታችን እና መደማመጣችን መመለስ አለበት ብለዋል።

መንግሥትም ኾነ የታጠቁ አካላት መደማመጥን መርህ አድርገው ለሕዝብ ሲሉ ወደ ሰላም መምጣት አለባቸው ነው ያሉት። ይህ እንዲሳካም እንደ ሃይማኖት አባት ኀላፊነታችንን መወጣት ይጠበቅብናል ብለዋል። የሃይማኖት አባቶች እና የሀገር ሽማግሌዎች ቁርጠኛ ኾነን ለሰላም ዘብ መቆም አለብን ነው ያሉት።

ሌላው የውይይቱ ተሳታፊ የሀገር ሽማግሌ አቶ ዳኝነት ተገኘ ዘላቂ ሰላም እንዲመጣ ከተፈለገ ከልቡ ለሰላም የቆመ የሀገር ሽማግሌ እና የሃይማኖት አባት ያስፈልጋል ብለዋል። በመገፋፋት እና በመጠላለፍ አብሮ መኖር የለም ነው ያሉት አቶ ዳኝነት።

መንግሥት ተሰሚነት ያላቸውን የኅብረተሰብ ክፍሎች ታች ድረስ ወርዶ እያወያየበት ያለው ተግባር ጥሩ ነው ብለዋል።

በዋዘኝነት ሀገር ወደ ኋላ ይቀራል፤ ልማትም ይደናቀፋል ነው ያሉት። ዝርፊያ እና እንግልት መቅረት አለበት፤ ሰው ሠርቶ መብላት አለበት ያሉት የሀገር ሽማግሌው ይህ እውን እንዲኾን የሀገር ሽማግሌዎች ኀላፊነታችንን እንወጣለን ብለዋል።

በመድረኩ ላይ የተገኙት የባሕር ዳር ከተማ አሥተዳደር ተቀዳሚ ምክትል ከንቲባ ጎሹ እንዳላማው የሀገራችን ሰላም በዘላቂነት ለማረጋገጥ ከሃይማኖት አባቶች እና ከሀገር ሽማግሌዎች ጋር መምከር የግድ ነው ብለዋል።

አሁን ላይ ያለውን የጸጥታ ችግር ለመቅረፍም ከልብ በመነጨ አኳዃን መምከር እና መወያየት ይኖርብናል ነው ያሉት። ትናንት የነበረውን ሰላማችን ባስቸኳይ መመለስ ካልቻልን ሕዝባችን ወደ ከፋ ችግር መግባቱ የማይቀር ነው ብለዋል። የሰላሙ ባለቤት ደግሞ በዋናነት ሰፊው ሕዝብ እንደኾነም ገልጸዋል።

ሰላምን ለመንግሥት ብቻ መተው የማይታሰብ በመኾኑ ሁሉም በያገባኛል ስሜት ኀላፊነቱን መወጣት ይኖርበታል ብለዋል። የሃይማኖት አባቶች እና የሀገር ሽማግሌዎች ደግሞ ድርሻቸው ትልቅ መኾን አለበት ነው ያሉት።

“የሃይማኖት አባቶች እና የሀገር ሽማግሌዎች በድፍረት ደም መፍሰስ ሊቆም ይገባል ማለት አለባችሁ” ብለዋል።
የአማራ ሕዝብ ልጆች ወገናቸውን ከድህነት እና ኋላቀርነት ማሻገር ነው ያለባቸው እንጅ ለከፍ ችግር መዳረግ አያስፈልግም ነበር ነው ያሉት። በመገዳደል የአማራን ሕዝብ ችግር መቅረፍ አይቻልም ብለዋል።

ከልብ በመነጨ ኀላፊነት መነጋገር እና ማሰብ እንደ ሕዝብ ይጠበቅብናል ነው ያሉት አቶ ጎሹ።

ዘጋቢ: ሰለሞን አንዳርጌ

የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን

Previous articleደቡብ ጎንደር ዞን የተጀመሩ የልማት ሥራዎች በተቀመጠላቸው ጊዜ እንዲጠናቀቁ እየሠራ ነው።
Next article“ከጥፋት መክሮ መመለስ የሃይማኖት አባቶች ተቀዳሚ ተግባር መኾን አለበት” የአማራ ክልል ፍትሕ ቢሮ ኀላፊ ብርሃኑ ጎሽም