ደቡብ ጎንደር ዞን የተጀመሩ የልማት ሥራዎች በተቀመጠላቸው ጊዜ እንዲጠናቀቁ እየሠራ ነው።

34

ደብረ ታቦር፡ ግንቦት 02/2017 ዓ.ም (አሚኮ) የክልሉ እና የዞን የሥራ ኀላፊዎች በሐሙሲት ከተማ አሥተዳደር እና በአምበሳሜ ከተማ የተሠሩ መሠረተ ልማቶችን ተመልክተዋል።

ከተመለከቷቸው መሠረተ ልማቶች ውስጥ ደግሞ ከሐሙሲት እስቴ እየተሠራ የሚገኘው የአስፋልት መንገድ፣ የሐሙሲት የውስጥ ለውስጥ የመንገድ ግንባታ እና በዶሮ ርባታ የተሠማሩ ወጣቶች ይገኙበታል።

የደቡብ ጎንደር ዞን ዋና አሥተዳዳሪ ጥላሁን ደጀኔ በዞኑ ትኩረት ከተሰጣቸው ጉዳዮች የወጣቶች የሥራ እድል አንዱ መኾኑን ገልጸዋል። በበጀት ዓመቱ ከእቅዱ 83 በመቶ ለሚኾኑ ወጣቶች የሥራ እድል ተፈጥሮላቸዋል ብለዋል። የውጭ ሀገር የሥራ ሥምሪት ደግሞ ትኩረት ከተሰጣቸው ውስጥ አንዱ ነው። ወደ ሥራ ለገቡ ወጣቶችም ከመሥሪያ ቦታ ጀምሮ ድጋፍ እየተደረገ መኾኑን ገልጸዋል።

በአምበሳሜ ከተማ በቀን ከሶስት ሺህ በላይ እንቁላል ማቅረብ የሚችሉ ወጣቶችን መፍጠር መቻሉን ገልጸዋል።

የሐሙሲት እስቴ መንገድ እንዲጠናቀቅ ከማኅበረሰቡ ጋር በመቀናጀት ትኩረት ተሠጥቶ እየተሠራ መኾኑንም ገልጸዋል።

የመንገዱ መገንባት ከፍተኛ የግብርና ምርቶች አምራች የኾኑትን የእስቴ እና ደራ ወረዳዎችን ምጣኔ ሀብታዊ እና ማኅበራዊ መሥተጋብር ይበልጥ የሚያስተሳስር ነው።

የሐሙሲት እስቴ መንገድ የዓመታት የሕዝብን ጥያቄ ችግር የፈታ መኾኑን የገለጹት ደግሞ የደራ ወረዳ ዋና አሥተዳዳሪ እስቲበል ጓዴ ናቸው።

የማኅበረሰቡ ትብብር ለመንገዱ መጠናቀቅ ትልቅ አቅም እንደነበረው ገልጸዋል። ወረዳው እንደ ጤፍ፣ በቆሎ፣ ስንዴ፣ ቦሎቄ እና ቡና የመሳሰሉ ሰብሎችን የሚያመርት ትርፍ አምራች እና ከፍተኛ የእንስሳት ሀብት የሚገኝበት በመኾኑ የመንገዱ መጠናቀቅ ምርትን በፍጥነት ወደ ገበያ ለማቅረብ እድል ፈጥሯል ብለዋል። ወላድ እናቶች በፍጥነት በጤና ተቋማት አገልግሎት እንዲያገኙ ኾናል ነው ያሉት።

ሌላኛው በወረዳው ትኩረት የተሰጠው የወጣቶች ሥራ እድል ነው። አንድ ማኅበር ብቻ ከ3 ሺህ በላይ ዶሮዎችን እያረባ ጫጩቶችን እና እንቁላል ለገበያ እያቀረበ ይገኛል። ለተደራጁ ወጣቶች የመስሪያ ቦታ ሸዶችን ጭምር ድጋፍ ማድረጋቸውን ገልጸዋል። ተሞክሮውን ዝቅተኛ ገቢ ላላቸው የመንግሥት ሠራተኞች የማስፋት ሥራ እየተሠራ መኾኑንም ገልጸዋል።

የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን

Previous article“የአማራን ሕዝብ ሰላም እና ደኅንነት ከመቼውም ጊዜ በላይ የምናስጠብቅበት ምዕራፍ ላይ ነን” ኮሚሽነር ዘላለም መንግሥቴ
Next article“እንደ ሕዝብ ከልብ በመነጨ ኀላፊነት መነጋገር እና ማሰብ ይጠበቅብናል” ተቀዳሚ ምክትል ከንቲባ ጎሹ እንዳላማው