
ባሕር ዳር: ግንቦት 02/2017 ዓ.ም (አሚኮ) የአማራ ክልል ፖሊስ ኮሚሽን የ100 ቀናት ዕቅድ ትውውቅ እና የለውጥ ሥራዎች ላይ ውይይት እያደረገ ነው።
በውይይቱ የአማራ ክልል ፖሊስ ኮሚሽን ኮሚሽነር ዘላለም መንግሥቴ፣ ምክትል ኮሚሽነሮች፣ ስትራቴጂክ መሪዎች፣ የዞን እና የከተማ አሥተዳደር ፖሊስ መምሪያ ኀላፊዎች ተገኝተዋል።
በውይይቱ ላይ መልዕክት ያስተላለፉት የአማራ ክልል ፖሊስ ኮሚሽን ኮሚሽነር ዘላለም መንግሥቴ አሁን ላይ የፖሊስ የመነሳት እና የከፍታ ዘመን ጀምሯል ብለዋል። የአማራ ፖሊስ ጠንካራ የፖሊስ ሥራ የሚያሳይበት፣ ተሞክሮ የሚቀሰምበት፣ ልምድ የሚወሰድበት እንዲኾን ማድረግ ይገባናል ነው ያሉት።
ከዓመታት በፊት የአማራ ፖሊስ “በማኅበረሰብ አቀፍ ፖሊስ” እንደ ኢትዮጵያ ተሞክሮ የሚወድበት እንደነበርም አስታውሰዋል። የአማራ ፖሊስ ወደ ቀደመ ቁመናው፣ ከፍታው እና ጀግንነቱ እንዲመለስ ይሠራል ነው ያሉት።
የሚከበር፣ የሚፈራ፣ የሚወደድ እና በሕዝብ ዘንድ የሚታመን ለማድረግ የሁላችንም ርብርብ ያስፈልጋል ብለዋል። በለውጡ የተሻለ ሥራ ሠርተን የአማራ ክልልን ሕዝብ የምንክስበት፣ የክልሉ መንግሥት በእኛ ላይ የጣለውን እምነት በተግባር የምናሳይበት፣ ተልዕኳችንን በብቃት የምንወጣበት መኾን አለበት ነው ያሉት።
“የአማራን ሕዝብ ሰላም እና ደኅንነት ከመቼውም ጊዜ በላይ የምናስጠብቅበት ጊዜ እና ምዕራፍ ላይ ነን” ያሉት ኮሚሽነሩ ለውጡን በሚገባ መተግበር እና ለሕዝብ ሰላም እና ደኅንነት በጋራ መሥራት ይገባል ብለዋል።
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!