“ለክልሉ ሕዝብ ሁለንተናዊ ተጠቃሚነት ሲባል ለውይይት ቅድሚያ መስጠት ይገባል” ድረስ ሳህሉ (ዶ.ር)

14

ባሕር ዳር፡ ግንቦት 01/2017 ዓ.ም (አሚኮ) በሰሜን ጎጃም ዞን “የጥፋት እጆችና መዘዞቹ” በሚል መሪ መልዕክት የክልልና የዞን ከፍተኛ የሥራ ኀላፊዎች በተገኙበት ከመንግሥት ሠራተኞች ጋር ውይይት ተካሂዷል። በምክትል ርእሰ መሥተዳድር ማዕረግ የገጠር ዘርፍ አስተባባሪና የግብርና ቢሮ ኀላፊ ድረስ ሳህሉ (ዶ.ር) በተሳሳተ መንገድ ጫካ የገቡ ኃይሎች ለክልሉ ሕዝብ ሁለንተናዊ ተጠቃሚነት ሲባል በሀሳብ ልዕልና በማመን ለውይይት ቅድሚያ ሊሰጡ ይገባል ብለዋል።

የርእሰ መሥተዳድሩ የኢኮኖሚ ዘርፍ አማካሪ ቀለመወርቅ ምህረቴ ሕዝቡ የገጠመው መከራና ሀዘን በቃ ሊባል እና ድርጊቱም ሊወገዝም ይገባል ብለዋል። ክልሉ የገጠመውን የጸጥታ ችግር ለመፍታት ሁላችንም ድርሻ አለብን ያሉት አቶ ቀለመወርቅ መንግሥት የሰጠውን የሰላም አማራጭ በመጠቀም ለምክክርና ለኅብረተሰቡ ተጠቃሚነት መረጋገጥ ሠራተኞች የበኩላቸውን ድርሻ እንዲወጡ አሳስበዋል።

የሰሜን ጎጃም ዞን ዋና አሥተዳዳሪ አሰፋ ጥላሁን በክልሉ በገጠመው የጸጥታ ችግር ምንም ዓይነት የፖለቲካ አጀንዳ ሳይኖራቸው በርካታ ንጹሐን የጥቃት ሰለባ መኾናቸውን አንስተዋል። ይህ ሊወገዝ የሚገባው ጉዳይ ነው ብለዋል።

የማኅበረሰቡ ችግር የሁላችንም ጉዳይ ነው ያሉት አሥተዳዳሪው የጸጥታ ችግሩ ኅብረተሰቡን ለበርካታ ማኅበራዊና ኢኮኖሚያዊ ችግሮች ተጋላጭ አድርጎታል ነው ያሉት። ሠራተኞች ሰላምን በማስፈን ላይ ትኩረት ማድረግ እንደሚኖርባቸውም አመላክተዋል።

የሰሜን ጎጃም ዞን ብልጽግና ፓርቲ ቅርንጫፍ ጽሕፈት ቤት ኀላፊ ማስተዋል አሰሙ የሕዝብን የመልካም አሥተዳደር እና የልማት ጥያቄዎችን ለመፍታት የመንግሥት ሠራተኞች አበርክቶ ከፍተኛ መሆኑን ገልጸዋል።

በዞኑ እየተደረጉ ያሉ ውይይቶች የጸጥታ ችግርን በመፍታትና ሰላምን ማረጋገጥ የማኅበረሰቡን የመልካም አሥተዳደርና የልማት ጥያቄዎች እንዲፈቱ የሚያስችሉ

ናቸው ብለዋል። ከአማራ ክልል ብልጽግና ፓርቲ ቅርንጫፍ ጽሕፈት ቤት የተገኘው መረጃ እንደሚያመላክተው የውይይቱ ተሳታፊዎች ሰላምን ለማረጋግጥ በሚደረገው ጥረት የበኩላቸውን ድርሻ እንደሚወጡ ተናግረዋል።

የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን

Previous articleየተፈጠረውን አንጻራዊ ሰላም ወደ ዘላቂ ሰላም ለመቀየር የመንግሥት ሠራተኞች የበኩላቸውን ሚና እንዲወጡ ተጠየቀ።
Next article“የአማራን ሕዝብ ሰላም እና ደኅንነት ከመቼውም ጊዜ በላይ የምናስጠብቅበት ምዕራፍ ላይ ነን” ኮሚሽነር ዘላለም መንግሥቴ