የተፈጠረውን አንጻራዊ ሰላም ወደ ዘላቂ ሰላም ለመቀየር የመንግሥት ሠራተኞች የበኩላቸውን ሚና እንዲወጡ ተጠየቀ።

17

ባሕር ዳር፡ ግንቦት 01/2017 ዓ.ም (አሚኮ) በአማራ ክልል ከተማ ልማት ዘርፍ የሚገኙ የመንግሥት ሠራተኞች ”የጥፋት እጆች እና መዘዞቹ ”በሚል መልዕክት ተወያይተዋል። የአማራ ክልል መሬት ቢሮ ኀላፊ ሲሳይ ዳምጤ የልዩነት ሐሳብ አለኝ ብሎ በዱር በገደሉ እየተንቀሳቀሰ ያለው ጽንፈኛ ኀይል በክልሉ በሁሉም አካባቢ የአማራን ሕዝብ የማይመጥን በደል አድርሷል ነው ያሉት፡፡

ይህ ጽንፈኛ ኀይል ወደ ቀልቡ እንዲመለስ በተደጋጋሚ በክልሉ እና በፌዴራል መንግሥት የሰላም ጥሪ ተደርጓል ያሉት አቶ ሲሳይ በሃይማኖት አባቶች፣ በሀገር ሽማግሌዎች እና በተጽዕኖ ፈጣሪ ግለሰቦችም የጥፋት ቡድኑ ወደ ሰላም እንዲመጣ ጥሪ ተደርጎለታል ብለዋል፡፡ ጥሪውን የተቀበሉ በርካታ ታጣቂዎችም ወደ ሰላም መመለሳቸውን አስታውሰዋል፡፡

በክልሉ ያለው ሰላም እየተሻሻለ የመጣ መኾኑን ገልጸዋል። በየደረጃው ያለው የማኅበረሰብ ክፍል የጥፋት ኀይሉ በሕዝብ እና ንብረት ላይ ያደረሰውን ሰብዓዊ ግፍ እና ቁሳዊ ኪሳራ በመመልከት እንዲያወግዘው ያለመ ውይይት እየተደረገ ነው ብለዋል፡፡ በክልሉ የመጣውን አንጻራዊ ሰላም ወደ ዘላቂ ሰላም ለመቀየር የመንግሥት ሠራተኞች የበኩላቸውን ሚና ሊወጡ እንደሚገባም አመላክተዋል።

ከአሁን በፊት በተለያዩ አካባቢዎች ይህ ቡድን ያደረሰውን ጉዳት የተመለከቱ በርካታ የማኅበረሰብ ክፍሎች ጽንፈኛውን ቡድን ማውገዛቸውን አብራርተዋል፡፡ ጽንፈኛው ኀይል በክልሉ የትውልድ ቅብብሎሹን እንዳይኖር መማር ማስተማሩ እንዲቆም ማድረጉን ተናግረዋል። ፖለቲካ እና ትምህርት እንደማይገናኙ አመላክተዋል። ይህ ድርጊት የቡድኑን የጥፋት ጉዞ ያሣያል ነው ያሉት፡፡

የውይይቱ ተሳታፊዎችም ጽንፈኛ ቡድኑ እየሠራው ያለውን ተግባርም አጥብቀው እንደሚያወግዙት ተናግረዋል።

ዘጋቢ፦ ሙሉጌታ ሙጨ

የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን

Previous articleበክልሉ ዘላቂ ሰላም እንዲሰፍን የመንግሥት ሠራተኞች ሚና ከፍተኛ መኾን አለበት።
Next article“ለክልሉ ሕዝብ ሁለንተናዊ ተጠቃሚነት ሲባል ለውይይት ቅድሚያ መስጠት ይገባል” ድረስ ሳህሉ (ዶ.ር)