በክልሉ ዘላቂ ሰላም እንዲሰፍን የመንግሥት ሠራተኞች ሚና ከፍተኛ መኾን አለበት።

12

ደብረ ማርቆስ: ግንቦት 01/2017 ዓ.ም (አሚኮ) የምሥራቅ ጎጃም ዞን የመንግሥት ሠራተኞች “የጥፋት እጆች እና መዘዞቹ” በሚል መሪ መልዕክት ተወያይተዋል።

በውይይቱ ላይ የተገኙት በአማራ ክልል ምክር ቤት የግብርና፣ አካባቢ ጥበቃ እና ውኃ ሀብት ልማት ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ሰብሳቢ ከፍያለው ሙላቴ በክልሉ ዘላቂ ሰላም እንዲመጣ የመንግሥት ሠራተኞች ኀላፊነታቸውን ሊወጡ ይገባል ብለዋል።

ሕዝብን ያማረሩ ብልሹ አሠራሮችን መታገል ያስፈልጋል ያሉት ሰብሳቢው በቀጣይም የመንግሥት ሠራተኞች ሰላምን ከማጽናት ጎን ለጎን ፍትሐዊ አገልግሎት በመስጠት የሕዝብ አገልጋይነታቸውን በተግባር ማሳየት እንደሚጠበቅባቸው ተናግረዋል።

የምሥራቅ ጎጃም ዞን ብልጽግና ፓርቲ ቅርንጫፍ ጽሕፈት ቤት ኀላፊ ተስፋዬ በላይ በዞኑ ሰላምን ለማጽናት ከመንግሥት ሠራተኞች ጋር ሰፊ ውይይቶች መደረጋቸውን አስታውሰዋል ።

በዞኑ እየታዬ ያለውን አንጻራዊ ሰላም ዘላቂ ለማድረግ ሁሉም በየደረጃው በኀላፊነት ስሜት መሥራት እንደሚገባውም ተናግረዋል።

የውይይቱ ተሳታፊዎችም ግጭቱ ያመጣው ማኅበራዊ እና ኢኮኖሚያዊ ኪሳራ ኅብረተሰቡን ችግር ውስጥ ያስገባ መኾኑን ተናግረዋል። ከእርስ በርስ መጠፋፋት ወጥተን ሕዝብን በታማኝነት የምናገለግልበት እና ፊታችንንም ወደ ልማት ማዞር የሚገባን ጊዜ ላይ እንገኛለን ነው ያሉት።

የዞኑ የመንግሥት ሠራተኞች ለዘላቂ ሰላም መስፈን የሚጠበቅባቸውን ሁሉ ለመወጣት ዝግጁ መኾናቸውንም ተናግረዋል።

የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን

Previous article“ቀድሞ የበቀለን ጆሮ በኋላ የመጣ ቀንድ ሊቀድመው ይችላል” ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ.ር)
Next articleየተፈጠረውን አንጻራዊ ሰላም ወደ ዘላቂ ሰላም ለመቀየር የመንግሥት ሠራተኞች የበኩላቸውን ሚና እንዲወጡ ተጠየቀ።