
ባሕር ዳር፡ ግንቦት 01/2017 ዓ.ም (አሚኮ) የአማራ ሚዲያ ኮርፖሬሽን ከአፍሪካ አመራር ልህቀት አካዳሚ ጋር በመተባበር “የመሪነት ጥበብ” በሚል መሪ ሃሳብ ለኮርፖሬሽኑ መሪዎች ሲሰጥ የቆየውን ሥልጠና አጠናቅቋል፡፡ ሥልጠናው የዕውቀት፣ የክህሎት እና የቴክኖሎጂ ክፍተትን ከመሙላት ባሻገር ዘመኑን የዋጀ አገልግሎት ለመስጠት የሚያስችል ነው ተብሏል፡፡
በሥልጠናው ማጠናቀቂያ መርሐ ግብር ላይ አስተያየታቸውን የሰጡት ሠልጣኞች የሥልጠናው ርእሰ ጉዳዮች ዘመኑን የዋጁ እና ተቋማዊ ተልዕኮን ለመወጣት የሚያግዙ ናቸው ብለዋል፡፡ አሚኮ በቴክኖሎጂ የዘመነ እና አሁን ያለውን የዓለም የሚዲያ ዕድገት ታሳቢ ያደረጉ ሥራዎች ለመሥራት ዝግጅቶች እያደረገ እንደኾነ ያነሱት ሠልጣኞቹ በየደረጃው ያለውን የሰው ኀይል በዕውቀት እና ክህሎት ለማብቃት የሚደረገው ጥረትም አበረታች ነው ብለዋል፡፡
ሥልጠናው በተለይም በሙያቸው የተሻለ ግንዛቤ እንዲኖራቸው፣ ዓለም አቀፋዊ ነባራዊ ሁኔታውን እንዲረዱ ያደረገ እና ለሥራቸው አጋዥ የኾኑ እይታዎችን ያገኙበት መኾኑን ጠቅሰዋል። በቀጣይም ራሳቸውን ለማብቃት፣ ለማሻሻል እና ተወዳዳሪ ለመኾን ዝግጅት የሚያደርጉበት እንደሚኾን አንስተዋል፡፡
የአማራ ሚዲያ ኮርፖሬሽን ዋና ሥራ አሥፈጻሚ ጋዜጠኛ ሙሉቀን ሰጥየ ኮርፖሬሽኑ ከአፍሪካ አመራር ልህቀት አካዳሚ ጋር በመተባበር ለመሪዎች የተሰጠው ሥልጠና የኮርፖሬሽኑን ስትራቴጂክ ዕቅዶች ለማሳካት እና ኮርፖሬሽኑ የተጣለበትን ኀላፊነት ለመወጣት የሚያግዝ ነው ብለዋል፡፡ ከአሚኮ ጋር በመተባበር ሥልጠናውን ለሰጠው የአፍሪካ አመራር ልህቀት አካዳሚም ምሥጋና አቅርበዋል፡፡
ሥልጠናውን የሰጡት የአፍሪካ አመራር ልህቀት አካዳሚ ፕሬዝዳንት ዛዲግ አብርሃ ሚዲያው ተፅዕኖ ፈጣሪ ኾኖ የሕዝብን እውነተኛ ማንነት በበጎ መግለጽ እስኪችል ድረስ አልሞ መሥራት ያስፈልጋል ብለዋል፡፡
አሁን ላይ በበጎም ይሁን በመጥፎ የምናውቃቸው ሀገራት የሚዲያ ተፅዕኖ ውጤት ናቸው ያሉት አቶ ዛዲግ “አሚኮን መለወጥ እና ማሻሻል ክልሉን በሁለንተናዊ መንገድ ማሻሻል ነው” ብለዋል፡፡ የሰው ኀይሉን በሥልጠና ለማብቃት የሚደረገውን ጥረት እንደሚደግፉም ተናግረዋል፡፡
ዘጋቢ፡- ታዘብ አራጋው
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን