
ወልድያ: ግንቦት 01/2017 ዓ.ም (አሚኮ) በወልድያ ከተማ አሥተዳደር “የጥፋት እጆች እና መዘዞቹ” በሚል መሪ መልዕክት ከመንግሥት ሠራተኞች ጋር ውይይት እየተካሄደ ነው። በከተፈጠረው የጸጥታ ችግር ምክንያት የመንግሥት ሠራተኞች እየታገቱ እና ገንዘብ እየተጠየቀባቸው መኾኑን ተናግረዋል። ባለሙያዎች እና መሪዎች ለግድያ ሰለባ እየኾኑ እንደኾነም ገልጸዋል።
ግብር በአግባቡ ሰብስበን ልማት ማልማት አልቻልንም፤ ኅብረተሰባችንን በነጻነት እንዳናገለግል ኾነናል ብለዋል። የዚህ ሁሉ ችግር መንስኤ የሰላም መደፍረስ ነውና እንደመንግሥት ሠራተኛ የከተማችን ሰላም ለማጽናት የድሻችን ልንወጣ ይገባል ነው ያሉት። የወልድያ ከተማ አሥተዳደር ብልጽግና ፓርቲ ቅርንጫፍ ጽሕፈት ቤት ኀላፊ ተስፋዬ ገብሬ የመንግሥት ሠራተኞች ኅብረተሰቡን ስለ ሰላም ግንዛቤ የመፍጠር ተግባር ማከናወን ይጠበቅባቸዋል ብለዋል።
የወልድያ ከተማ አሥተዳደር ተቀዳሚ ምክትል ከንቲባ ዱባለ አብራሬ የመልካም አሥተዳደር ጉድለት አንዱ የቅሬታ ምንጭ በመኾኑ መንግሥት ሠራተኞች በቅንነት እና በታማኝነት ኅብረተሰቡን ማገልገል አለባቸው ብለዋል። ወቅታዊ የጸጥታ ችግሩ የመንግሥት ሠራተኞችን በቀጥታ ተጠቂ እንደሚያደርግም ገልጸዋል። ወንድሞቻቸውን በመምከር ወደ ሰላም እንዲመጡ ሊያደርጉም ይገባል ነው ያሉት።
የዘመን ኮንስትራክሽን ምክትል ሥራ አሥፈጻሚ ደጀኔ ሽባባው መንግሥት ሠራተኞች የችግሩን ምንጭ ተረድተው ለሰላም መሥራት ይገባቸዋል ብለዋል። ከዚህ በኋላ በሁለት ቢላዋ መብላት የለም ያሉት ሥራ አሥፈጻሚው ለጽንፈኞች መረጃ አቀባይ እና ሎጅስቲክ እያደረሱ ሰላማዊ ሰው መስሎ መኖር አይቻልም ነው ያሉት። የመንግሥት ሠራተኞች ከዚህ መሰል ድርጊት እንዲታቀቡ አሳስበዋል።
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን