የአዊ ብሔረሰብ አሥተዳደር ወደ አንፃራዊ ሰላም እየተመለሰ መኾኑን ብሔረሰብ አሥተዳደሩ አስታወቀ።

42

እንጅባራ: ሚያዝያ 30/2017 ዓ.ም (አሚኮ) ርእሰ መሥተዳድር አረጋ ከበደ ከአዊ ብሔረሰብ አሥተዳደር ነዋሪዎች ጋር በእንጅባራ እየተወያዩ ነው። በውይይቱ የአማራ ክልል ፖሊስ ኮሚሽን ኮሚሽነር ዘላለም መንግሥቴ፣ የአዊ ብሔረሰብ አሥተዳደር ዋና አሥተዳዳሪ ቴዎድሮስ እንዳለው፣ በሀገር መከላከያ ሠራዊት የምሥራቅ እዝ የ302 ኮር አዛዥ ብርጋዴር ጄኔራል መለስ መንግሥቴን ጨምሮ ሌሎች ከፍተኛ የሥራ ኀላፊዎች ተገኝተዋል።

በውይይቱ ላይ መልዕክት ያስተላለፉት የአዊ ብሔረሰብ አሥተዳደር ዋና አሥተዳዳሪ ቴዎድሮስ እንዳለው ኢትዮጵያ በጋራ ሕልም የተጋመዱ ብሔሮች፣ ብሔረሰቦች እና ሕዝቦች አካላዊ፣ ምናባዊ እና ሥርዓታዊ ውቅር ፈጥረው፣ በኅብረ ብሔራዊ ማንነታቸው ተጋምደው የሚኖሩባት የጋራ ሀገራችን ናት ብለዋል።

በኢትዮጵያ ሀገረ መንግሥት ግንባታ ሂደትም መላው የኢትዮጵያ ብሔሮች፣ ብሔረሰቦች እና ሕዝቦች አስተዋጽኦ ማድረጋቸውን ገልጸዋል። የአማራ ክልል ሕዝብም ለኢትዮጵያ የሀገረ መንግሥት ግንባታ ሂደት ገናና ታሪክ ያለው መኾኑን አንስተዋል። ከኢትዮጵያዊነት ማማው ከፍ እንዳለ የሚገኘው የአማራ ክልል ሕዝብ በሰሜኑ ጦርነት የተፈጠረውን ጦርነት ከሀገር መከላከያ ሠራዊቱ እና ከመላው የኢትዮጵያ ሕዝብ ጋር በመኾን መመከቱንም ተናግረዋል።

ከሰሜኑ ጦርነት በኋላ መንግሥት በቁልፍ አጀንዳነት የያዛቸውን የአማራ ክልል ሕዝብ ጥያቄዎችን በመንጠቅ ለአማራ ሕዝብ ቆሜያለሁ የሚል ታጣቂ ቡድን በክልሉ ላይ ከፍተኛ ጉዳት ማድረሱን ተናግረዋል። በዚህም የአማራ ክልል ሕዝብ ሰብዓዊ፣ ቁሳዊ እና ሥነ ልቦናዊ ጉዳት ደርሶበታል ነው ያሉት፡፡ ፖለቲካዊ፣ ማኅበራዊ እና ኢኮኖሚያዊ እድገቱ ወደ ኋላ እንዲመለስም ኾኗል ብለዋል።

የተፈጠረው የጸጥታ ችግር ያለፈ ገናና ታሪካችንን ጥላሸት ከመቀባቱም ባሻገር ዛሬያችንን በማበላሸት ለነጋችንም ጭምር የሚተርፍ ጠባሳ እየጣለ ነው ብለዋል። አርሶ አደሮች ያመረቱትን ምርት የፈለጉበት ቦታ ወስደው እንዳይሸጡ፣ የአርሶ አደሮችን ምርት፣ እሴት የሚጨምሩለት ፋብሪካዎች ግንኙነት ተቋርጧል ነው ያሉት፡፡

የመንግሥት አገልግሎት ሰጪ ተቋማት ወድመዋል፤ በሚሊዮን የሚቆጠሩ ተማሪዎች ከትምህርት ገበታ ተስተጓጉለዋል ብለዋል። ከማኅበረሰቡ የጨዋነት ባሕልና መገለጫ ያፈነገጡ መጥፎ ልምምዶች መንሰራፋታቸውንም ገልጸዋል። በጥቅሉ ማንሰራራት ላይ የነበረው ኢኮኖሚ እንዲንኮታኮት ኾኗል ነው ያሉት።

የሀገር መከላከያ ሠራዊት፣ የክልሉ የጸጥታ ኀይል፣ ሕዝቡ እና መሪዎች በጋራ በሠሩት የተቀናጀ ሥራ አንፃራዊ ሰላም መፈጠሩን ተናግረዋል። የሀገር መከላከያ ሠራዊት፣ የክልሉ የጸጥታ ኀይል እና የክልሉ ሕዝብ የከፈለው እና እየከፈለ ያለው መስዋዕትነት ታሪክ የሚዘክረው ይኾናል ብለዋል።

ጽንፈኛው ኃይል በአዊ ብሔረሰብ አሥተዳደር ላይም ከፍተኛ ጉዳት ማድረሱን ተናግረዋል። የክልሉ መንግሥት ለብሔረሰብ አሥተዳደሩ ልዩ ትኩረት በመስጠት ጽንፈኛው ኃይሉ የከፋ ጉዳት እንዳያደርስ ማድረጉን ገልጸዋል።

የሕዝቦችን የቆዬ የአብሮነት እሴት እንዳይሸረሽር እና የጽንፈኛው አካሄድ የከፋ እንዳይኾን ከፍተኛ ጥንቃቄ እና ጥበብ የተሞላበት ታሪካዊ አመራር መሰጠቱንም ተናግረዋል። ከየትኛውም ዋልታ ረገጥ እሳቤዎች የጸዳ አመራር በማደራጀት ብሔረሰብ አሥተዳደሩን መታደጉንም አንስተዋል።

የክልሉ መንግሥት ብሔረሰብ አሥተዳደሩ የሚጠይቃቸውን ጥያቄዎች ሁሉ አፋጣኝ ምላሽ እየሰጠ መኾኑን ተናግረዋል። በተሠራው ሥራ ብሔረሰብ አሥተዳደሩ በአንጻራዊ ሰላም ይገኛል ነው ያሉት።

በጽንፈኛው እጅ የተያዙ አካባቢዎች ነጻ እየወጡ ሰላም እየሰፋ መኾኑንም ተናግረዋል። ሕዝቡ በማንነቱ ጸንቶ እና በአብሮነቱ ተጋምዶ አሁን ላይ በጽንፈኛው ኃይል ላይ የበላይነትን ተቀዳጅቷል ነው ያሉት።

ከሰላም ጎን ለጎን ለልማት እና መልካም አሥተዳደር ሥራዎች ትኩረት ሰጥተው እየሠሩ መኾናቸውን ገልጸዋል።

በ2017 ዓ.ም ከ20 ሺህ ሄክታር መሬት በላይ የበጋ ስንዴ ማልማት መቻላቸውንም ተናግረዋል። የማኅበራዊ ልማት ሥራዎችን እያስቀጠሉ መኾናቸውን ገልጸዋል።

የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን

Previous articleየታጠቁ ኀይሎች የሰላም አማራጭን እንዲከተሉ ተጠየቀ።
Next articleየመንግሥት ሠራተኞች በቅንነት እና በታማኝነት ኅብረተሰቡን ማገልገል ይገባቸዋል።