
ባሕር ዳር:ሚያዝያ 30/2017 ዓ.ም (አሚኮ) በደቡብ ጎንደር ዞን ሐሙሲት ከተማ አሥተዳደር “ዘላቂ ሰላም ለሁለንተናዊ ብልጽግና” በሚል መልዕክት ሕዝባዊ የሰላም ውይይት ተካሂዷል። በውይይቱ የዞኑ እና የክልል የሥራ ኀላፊዎች ተገኝተዋል።
የአማራ ክልል ሰላም እና ጸጥታ ቢሮ ምክትል ኀላፊ በሪሁን መንግሥቴ እንዳሉት ባለፉት ዓመታት በሰሜኑ ጦርነት እና በክልሉ ውስጥ የተከሰተው የጸጥታ ችግር የክልሉን ነዋሪ ለማኅበራዊ፣ ለኢኮኖሚያዊ እና ለሥነ ልቦናዊ ቀውስ አጋልጧል። ሕጻናት እና እናቶች ደግሞ ይበልጥ ተጎጅ መኾናቸውን ገልጸዋል።
መንግሥት ከግጭት አትራፊ መኾን እንደማይቻል በመረዳት የሰላምን አማራጭ የተከተሉ በርካታ የታጠቁ ኀይሎች ወደ ማኅበረሰቡ እንዲቀላቀሉ ማድረጉን ገልጸዋል። በቀጣይም በክልሉ ሊደርስ የሚችለውን ጉዳት ለመቅረፍ መንግሥት ለሰላም ዝግጁ መኾኑን ነው የገለጹት።
የሰላምን አማራጭ በማይከተሉት ላይ ደግሞ የሕግ ማስከበር ሥራው ተጠናክሮ ይቀጥላል ብለዋል። አሁን ለተገኘው ሰላም የማኅበረሰቡ ድርሻ ከፍተኛ እንደነበርም ነው የገለጹት። በጫካ የሚገኙ ኀይሎች በኀይል የሚመለስ ጥያቄ እንደሌለ ተገንዝበው የሰላም አማራጭን እንዲመርጡ ጥሪ አቅርበዋል።
የሃይማኖት አባቶች፣ የሃገር ሽማግሌዎች፣ ወጣቶች እና እናቶች የታጠቁ አካላት የሰላም አማራጭን እንዲከተሉ እንዲመክሩ ጠይቀዋል።
የደቡብ ጎንደር ዞን ዋና አሥተዳዳሪ ጥላሁን ደጀኔ እንደገለጹት ደግሞ ባለፉት ሁለት ዓመታት በክልሉ በተከሰተው የጸጥታ ችግር ጉዳት ደርሷል። ዜጎች እየታገቱ ከፍተኛ ገንዘብ እንዲከፍሉ ተደርጓል፤ በዞኑ 500 ሺህ ተማሪዎችም ከትምህርት ገበታ ውጭ ኾነዋል ብለዋል።
በተሠራው ሥራም የሰላም አማራጭን የመረጡ የታጠቁ ኀይሎችን ወደ ማኅበረሰቡ እንዲቀላቀሉ መደረጉን ነው የገለጹት። የሰላም አማራጭን በማይከተሉ አካላት ላይ ደግሞ የሕግ የበላይነትን የማረጋገጥ ሥራ እየተሠራ ይገኛል ብለዋል።
ከሰላም ማረጋገጥ ባለፈ በዞኑ የተለያዩ የልማት ሥራዎች እየተከናወነ መኾኑን ገልጸዋል። ለአርሶ አደሮች ግብዓት በወቅቱ እንዲቀርብ ተደርጓል ብለዋል። በ2016 ዓ.ም ከ680 ሺህ በላይ ኩንታል ለአርሶ አደሮች መሠራጨቱን ያነሱት አሥተዳዳሪው በዚህ ዓመትም በዞኑ በቂ ግብዓት ለማሠራጨት ቅድመ ዝግጅት እየተደረገ መኾኑን ገልጸዋል።
ክልሉ ወደ ተሟላ ሰላም እንዲመለስ እና ማኅበረሰቡም መደበኛ ሥራውን እንዲያከናውን ማኅበረሰቡ ለሰላም ዘብ እንዲቆሙ አሳስበዋል።
የክልሉን የጸጥታ ችግር በአጭር ጊዜ በራስ አቅም ለመፍታት እየተሠራ መኾኑን ያነሱት ደግሞ የአማራ ክልል ፖሊስ ኮሚሽን ኮሚሽነር አማካሪ አበረ ዓለሙ ናቸው። ወደ ተሟላ ሰላም ለመመለስ ደግሞ ሙሉ የሕዝብ ተሳትፎ ያስፈልጋል ብለዋል። ማኅበረሰቡ በየአካባቢው ከሚገኘው የጸጥታ መዋቅር ጎን እንዲቆም ጠይቀዋል።
በደቡብ ጎንደር ዞን የሐሙሲት ከተማ አሥተዳደር ምክትል ከንቲባ ተመስገን የሽዋስ ባለፉት ሁለት ዓመታት በተከሰተው የጸጥታ ችግር የከተማዋ ነዋሪ ለማኅበራዊ እና ኢኮኖሚያዊ ቀውስ መጋለጡን ገልጸዋል። አሁን ላይ የተገኘውን አንጻራዊ ሰላም በዘላቂነት ለማረጋገጥም ከማኅበረሰቡ ጋር እየተሠራ መኾኑን ገልጸዋል።
የልማት እና የመልካም አሥተዳደር ጥያቄዎች በወቅቱ አለመፈታታቸው አሁን ላጋጠመው ችግር መንስዔዎች መኾናቸውን በተሳታፊዎች ተነስቷል።
መንግሥት የሕዝብ ጥያቄዎችን በወቅቱ እንዲመልስ፣ የተፈናቀሉ ዜጎች ወደ ነበሩበት እንዲመለሱ፣ ፍትሐዊ ልማት እንዲኖር፣ ጫቃ የገቡ ወገኖችን ጥያቄዎች አሁንም ማየት እንደሚገባ እና ለወጣቶች የሥራ እድል ፈጠራ ትኩረት እንዲሰጥ በተሳታፊዎች ተጠይቋል።
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን