“የክልል እና የፌዴራል መንግሥታት አደጋ ደርሶ ሪፖርት ከመቀበላቸው በፊት ቀድመው ተጨንቀው ቢሠሩ ጥሩ ነው፡፡” የሸዋሮ ቢት ከተማ አስተዳደር ከንቲባ

232

ባሕር ዳር፡ ግንቦት 12/2012 ዓ.ም (አብመድ) ከዚህ በፊት ተደጋጋሚ የጎርፍ አደጋ የተፈታተናቸው ከተሞች ዘላቂ መፍትሔ ስላልተሰጣቸው ዘንድሮም ስጋት አድሮባቸዋል፡፡ የሸዋሮ ቢት እና የወልድያ ከተማ አስተዳደሮች ነዋሪዎች ከፍተኛ የጎርፍ ተጋላጭነት ስጋት እንዳለባቸው ለአብመድ ተናግረዋል፡፡ አብመድ ባለፉት ዓመታት በተጠቀሱት ከተሞች ያጋጠሙ የጎርፍ አደጋዎችንና መሠራት የነበረባቸው የቅድመ መከላከል ሥራዎችን ሲዘግብ ኖሯል፡፡ ዘንድሮም የሁለቱ ከተሞች ነዋሪዎች መንግሥት ችግር ከመድረሱ በፊት ቀድሞ መፍትሔ እንዲፈልግ እየጠየቁ ነው፡፡

የሸዋ ሮቢት ከተማ አስተዳደር ከከተቆረቆረችበት ጊዜ ጀምሮ በየዓመቱ የጎርፍ አደጋ እየተከሰተ በግለሰቦች እና በመንግሥት ንብረቶች እንዲሁም በመሠረተ ልማት ላይ ከፍተኛ ጉዳት ያደርሳል፡፡ ከ2002 ዓ.ም ጀምሮ ደግሞ የጉዳቱ መጠን እየጨመረ ክረምት በገባ ቁጥር ነዋሪዎች ስጋት ውስጥ እየገቡ ነው፡፡ በቆቦ ወንዝ ላይ የተሠራው ድልድይ ከውኃው አቅም ጋር የተመጣጠነ ባለመሆኑ ውኃ ገንፍሎ ወደ ከተማ መሄዱ፣ ከተለያዩ ቦታዎች የሚሰባሰቡ ፍሳሾች በተገቢው መንገድ ወደ ወንዝ እንዲቀላቀሉ አለመደረጉ እና የሮቢት ወንዝ ድልድይ በማርጀቱ ምክንያት ውኃ ሰብሮ ወደ ከተማ በመግባቱ ነው በከተማ አስተዳደሩ በየዓመቱ ጎርፍ የሚከሰተው፡፡

ታዲያ ከድልድዮቹ ሥር የሚከማቸውን አሸዋ ከማውጣት ያለፈ ዘላቂ መፍትሔ ባለመሰጠቱ ክረምት በገባ ቁጥር በነዋሪዎች ዘንድ ከፍተኛ ስጋት እየተፈጠረ ነው፡፡ አስተያዬታቸውን ለአብመድ የሰጡ የከተማ አስተዳደሩ ነዋሪዎች በመጪው ክረምትም በከተማው ስድስት ቀበሌዎች የጎርፍ ተጋላጭነት ስጋት እንዳለባቸው ተናግረዋል፡፡ በመሆኑም መደበኛው የክረምት ወቅት ሰይገባ አስቸኳይ መፍትሔ እንዲፈለግላቸው ጠይቀዋል፡፡

ወልዲያ ከተማም በተደጋጋሚ የጎርፍ አደጋ የሚደርስባት ከተማ ነች፡፡ በተለይ ሙጋድ፣ ተክለ ሃይማኖት፣ አሬሮ፣ ጎማጣ እና ጉባላፍቶ የሚባሉ ሰፈሮች በተደጋጋ የጎርፍ አደጋ የሚከሰትባቸው ሰፈሮች ናቸው፤ ዘንድሮም ከፍተኛ ስጋት እንዳለባቸው የከተማዋ ነዋሪዎች ተናግረዋል፡፡ ነዋሪዎች ቆሻሻ በመጣል ነባር መፋሰሻዎችን መድፈናቸውና ተጀምረው ያልተጠናቀቁ አዳዲስ መፋሰሻዎች የስጋት ምንጭ መሆናቸውን ተናግረዋል፡፡ ከሳምንታት በፊት በጣለው ዝናብ መጠነኛ ጎርፍ መከሰቱን ተከትሎም በክረምቱ ከባድጎርፍ ሊከሰት እንደሚችል ነዋሪዎቹ ሰግተዋል፡፡ መንግሥት ለማኅበረሰቡ ግንዛቤ በመፍጠር እና ለጎርፍ የሚያጋልጡ ቦታዎችንና ሁኔታዎችን ማስተካከል ላይ በትኩረት ቢሠራ ስጋቱን ማስቀረት እንደሚቻልም ነዋሪዎቹ ተናግረዋል፡፡

‘‘ችግሩ ለምን ዘላቂ መፍትሔ አጣ?’’ ስንል ላቀረብነው ጥያቄ የከተማ አስተዳደሮቹ ከንቲባዎች ማብራሪያ ሰጥተዋል፡፡ የሸዋ ሮቢት ከተማ አስተዳደር ከንቲባ አካሉ ወንድሙ ችግሩ ከከተማ አስተዳደሩ አቅም በላይ መሆኑን አስታውቀዋል፡፡ ከተማ አስተዳደሩ በየዓመቱ አቅሙ በሚፈቅደው ልክ እየሠራ መሆኑንም ተናግረዋል፡፡ የከተማዋ ነዋሪዎችም ስጋት ስላለባቸው በየጊዜው ከፍተኛ ጥንቃቄ እንሚያደርጉ ከንቲባ አካሉ ተናግረዋል፡፡

ይሁን እንጂ የኢትዮጵያ መንገዶች ባለስልጣን ለችግሮች ዘላቂ መፍትሔ ባለመስጠቱ ምክንያት ከስጋት መላቀቅ እንዳልተቻለም ነው የተናገሩት፡፡ በከተማዋ የሚገኙ ሁለቱን ድልድዮች እንደገና መሥራት ዋነኛ መፍትሔ እንደሚሆን የተናገሩት ከንቲባው ድልድዮቹን ለመሥራት የተጀመሩ ተግባራት ቢኖሩም ባልታወቀ ምክንያት መቋረጣቸውን አስታውቀዋል፡፡ ከዚህ ባለፈም ችግሩን ለመፍታት የ52 ሚሊዮን ብር ፕሮጀክት ለክልሉ ቢያቀርቡም ከ800 ሺህ ብር በላይ ስለማይለቅ ሕዝቡን ከስጋት ነፃ ማድረግ እንዳልተቻለ ተናግረዋል፡፡ በመጪው ክረምት ከፍተኛ ስጋት መኖሩን ተናገሩት ከንቲባው “የክልል እና የፌደራል መንግሥታት አደጋ ደርሶ ሪፖርት ከመቀበላቸው በፊት ቀድመው ተጨንቀው ቢሠሩ ጥሩ ነው” ሲሉም አሳስበዋል፡፡

የፌዴራል መንገዶች ባለስልጣን ችግሩን አምኖ ለማስተካከል እየተሠራ መሆኑን አስታውቋል፡፡ የዓለም ገና መንገድ አውታር እና ደኅንነት ማኔጅመንት ዳይሬክተር ኡመር ሁሴን (ኢንጂነር) እንዳሉት የፍሳሽ ማስወገጃ ድልድዮቹ ቀደም ሲል የተሠሩ በመሆናቸው የዝናቡ መጠን በሚጨምር ጊዜ ችግሩ እንዲፈጠር ምክንያት ሆነዋል፡፡ እንደ ዳይሬክተሩ ገለጻ እንደዚህ ዓይነት ችግሮች ሲያጋጥሙ የአደጋ ቡድን በማቋቋም ጊዜያዊ መፍትሔ ይሰጣል፡፡ በዚህም መሠረት በመጪው ክረምት ጎርፍ ሊያስከትሉ የሚችሉ ቦታዎችን በመለየት ደለል የሞላቸውን ለማስተካከል አና ውኃው በድልድዮቹ እንዲያልፍ ለማድረግ የአደጋ በድኑ እየሠራ መሆኑን ተናግረዋል፡፡

በሁለቱ ወንዞች ላይ ዘላቂ መፍትሔ ለመስጠት እና በዘመናዊ መልክ ፍሳሽ ሊያስተናግዱ የሚችሉ ድልድዮችን ለመሥራት የዲዛን ሥራ እየተከናወነ መሆኑንም ነው ኢንጂነር ኡመር የተናገሩት፡፡ በተቻለ መጠን ችግሩን ለመፍታት እንደሚሠራ ከመናገር ባለፈ ግን የዘላቂ መፍትሔው አካል መቼ ተጀምሮ እንደሚጠናቀቅ ከመናገር ተቆጥበዋል፡፡

የወልድያ ከተማ አስተዳደር ከንቲባ አቶ መሐመድ ያሲን በሰጡት ምላሽ ደግሞ ከተማዋ በተራራ የተከበበች በመሆኗ ከተራራው የሚፈስስ ውኃ የሁል ጊዜ ስጋት መሆኑን ተናግረዋል፡፡ ይህንን ታሳቢ በማድረግም በዘላቂነት ከችግሩ ሊያወጣ የሚችል ጥናት ተሠርቶ የ160 ሚሊዮን ብር ፕሮጀክት እና ልዩ ልዩ ግንባታዎች መገንባት እንዳለባቸው ታውቋል፡፡ ነገር ግን በአጭር ጊዜ መሥራት ስለማይቻል የተደፈኑ ነባር መፋሰሻዎችን የመጥረግ፣ ኅብረተሰቡን ያሳተፈ የጽዳት ዘመቻ የመሥራት እና ባህላዊ ተፋሰሶችን በማሽን በመሥራት ወደ ትክክለኛው ወንዝ የማስገባት ተግባር እየተከናወነ እንደሚገኝ ተናግረዋል፡፡ ይህንንም እስከ ሰኔ 15/2012 ዓ.ም ለማጠናቀቅ እየተሠራ እንደሆነ ገልጸዋል፡፡

በክልሉ የት የት አካባቢዎች የጎርፍ አደጋ ሥጋት እንዳለ፣ ሕዝብ እና መንግሥት ችግሩን ቀድመው ለመከላከል ምን ዓይነት ጥንቃቄዎችን እየተደረጉ እንደሆነና ቀጣይ መደረግ ስለሚገባቸው ተግባራት ከአማራ ክልል አደጋ መከላከል፣ ምግብ ዋስትና እና ልዩ ድጋፍ የሚሹ አካባቢዎች ማስተባበሪያ ኮሚሽን ለማግኘት ያደረግነው ጥረት አልተሳካም፡፡ በኮሚሽኑ የቅድመ ማስጠንቀቂያና ምላሽ ዳይሬክተር ጀምበሩ ደሴ ማብራሪያ እንዲሰጡን በተደጋጋሚ ያደረግነው ጥረት አልተሳካም፤ መረጃዎችን እንዳገኘን የምናካትት ይሆናል፡፡

ዓለማቀፍ የአየር ሁኔታ ትንበያዎች እንደሚያመላክቱት የምሥራቅ አፍሪካ ሀገራት በመጪው ክረምት ከፍተኛ መጠን ያለው ዝናብ ይኖራቸዋል፤ ጎርፍና የመሬት መንሸራተትም የሚጠበቁ አደጋዎች ናቸው፡፡

ዘጋቢ፡- ደጀኔ በቀለ

ተጨማሪ መረጃዎችን
በቴሌግራም https://bit.ly/2wdQpiZ
ትዊተር https://bit.ly/37m6a4m
ዩቱዩብ https://bit.ly/38mpvDC ያገኛሉ፡፡

Previous articleአጎበር በየሦስት ዓመት ስለሚቀርብ መቸገራቸውን ነዋሪዎች ገለጹ፡፡
Next article“ኢትዮጵያ በዓባይ ውኃ አጠቃቀም ላይ እስካሁን ድረሰ ጥቅሟን የሚያስነካ ውል አልፈረመችም፤ ወደፊትም አትፈርምም፤ መፈረምም የለባትም፡፡” ዶክተር ይልማ ስለሺ