“የአዊ ሕዝብ ለሀገር እና ለአካባቢ ሰላም መኾን ትልቅ ዋጋ የሚሰጥ ነው” ርእሰ መሥተዳድር አረጋ ከበደ

49

ባሕር ዳር: ሚያዚያ: 30/2017 ዓ.ም (አሚኮ) ርእሰ መሥተዳድር አረጋ ከበደ ከአዊ ብሔረሰብ አሥተዳደር ነዋሪዎች ጋር በእንጅባራ እየተወያዩ ነው።

በውይይቱ የአማራ ክልል ፖሊስ ኮሚሽን ኮሚሽነር ዘላለም መንግሥቴ፣ የአዊ ብሔረሰብ አሥተዳደር ዋና አሥተዳዳሪ ቴዎድሮስ እንዳለው፣ በሀገር መከላከያ ሠራዊት ምሥራቅ ዕዝ የ302 ኮር አዛዥ ብርጋዴር ጄኔራል መለስ መንግሥቴ፣ የአማራ ሚዲያ ኮርፖሬሽን ዋና ሥራ አሥፈጻሚ አማካሪ ግዛቸው ሙሉነህን ጨምሮ ሌሎች ከፍተኛ የሥራ ኀላፊዎች ተገኝተዋል።

ውይይቱ በሰላም፣ በልማት እና በመልካም አሥተዳደር ላይ ትኩረቱን ያደረገ ነው። ርእሰ መሥተዳድር አረጋ ከበደ ለሰላም ወደ ሰላም በሯ ከተማ በሰላም መጥተናል ብለዋል። የአዊ ሕዝብ ከተፈጥሮ ጋር አስማምቶ፣ ተፈጥሮን ተንከባክቦ ራሱን በሚመቸው መንገድ የሚመራ ሕዝብ ነው ብለዋል።

የአዊ ሕዝብ ከሌላው ማኅበረሰብ ጋር ድር እና ማግ ኾኖ የሚኖር ሕዝብ መኾኑንም ተናግረዋል። “የአዊ ሕዝብ ለሀገር እና ለአካባቢ ሰላም መኾን ትልቅ ዋጋ የሚሰጥ ሕዝብ ነው” ብለዋል። ለሰላም ቀናዒ መኾኑንም አንስተዋል።

ለሀገር ሉዓላዊነት መስዋዕትነት የከፈለ፣ የቀደሙ አባቶችን ገድል የደገመ ትልቅ ሕዝብ መኾኑንም አንስተዋል። በሰሜኑ ጦርነት ወቅት የሀገርን ሉዓላዊነት ለመታደግ ከፍተኛ አስተዋጽኦ አድርጓል ነው ያሉት። በክልሉ በተፈጠረው የጸጥታ ችግርም በሰከነ መንገድ ሰላሙን የጠበቀ አስታዋይ ሕዝብ መኾኑንም ተናግረዋል።

ጽንፈኞች ሊፈጥሩት የነበረውን ያልተገባ ጉዳይ በጥበብ ያከሸፈ፣ አንድነቱን እና ሰላሙን የጠበቀ አካባቢ መኾኑንም ገልጸዋል። ችግር እንኳን ቢኖር በሰላም መፍታት አለበት ብሎ የሚያምን አስታዋይ ሕዝብ ነው ብለዋል።

የአካባቢው ለትምህርት ልዩ ትኩረት የሚሰጥ ነው ያሉት ርእሰ መሥተዳድሩ ትምህርት ከድህነት መውጫ፣ የእድገት ማረጋገጫ ነው ብሎ የሚያምን፣ ልጆቹን በልዩ ትኩረት የሚያስተምር ታላላቅ ምሁራንን ያፈራ መኾኑን ተናግረዋል።

የአዊ ሕዝብ ባሕሉን እና ወጉን ጠብቆ ለትውልድ ያስተላለፈ መኾኑንም ገልጸዋል። ሕግ አክባሪ፣ ሰላም ወዳድ፣ በፍትሕ እና በዳኝነት የሚያምን፣ ችግሮችን በሽምግልና ሥርዓት የሚፈታ፣ የኃይል አማራጭን የማያስቀድም ብልህ ሕዝብ ነው ብለዋል።

ለሰላም ያላቸውን ቀናዒነት፣ አስታዋይነት እና አርቆ አሳቢነት አጠናክረው እንዲጥልም አስገንዝበዋል።

የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous articleየተማሪ ተኮር የአገልግሎት መስጫ ግንባታዎች 22 ሺህ ተማሪዎችን ተጠቃሚ ያደርጋሉ።
Next articleየታጠቁ ኀይሎች የሰላም አማራጭን እንዲከተሉ ተጠየቀ።