
ባሕር ዳር፡ ሚያዝያ 30/2017 ዓ.ም (አሚኮ) “ኬር ኢትዮጵያ” በባሕር ዳር ከተማ በ11 ትምህርት ቤቶች ተማሪ ተኮር የተለያዩ የአገልግሎት መስጫ ግንባታዎችን አጠናቅቆ ለከተማው ትምህርት መምሪያ አስርክቧል፡፡ በርክክብ ሥነ ሥርዓቱ ላይ ያገኘናት የወተት በር አጠቃላይ አንደኛ ደረጃ ትምህርት ቤት የ7ኛ ክፍል ተማሪ ረድኤት አቤል የንጽህና መጠበቂያ የተለየ ክፍል ባለመኖሩ ተማሪዎች የወር አበባ ሲኖር እየተሸማቀቁ ከትምህርት ቤት ይቀሩ እንደ ነበር አስታውሳለች፡፡
ስለዚህ የልጃገረዶች የንጽህና መጠበቂያ ክፍል መገንባቱ ጠቀሜታው ከፍተኛ ነው ብላለች፡፡ የተሻለ ውጤት ለማምጣትም ተግታ እየተማረች መኾኗን ተናግራለች፡፡ በጠይማ አጠቃላይ አንደኛ ደረጃ ትምህርት ቤት የ8ኛ ክፍል ተማሪ አበራ አሰፋ እንዳለው በጠባብ ክፍል ውስጥ እየተማሩ ስለሚገኙ ትምህርቱን ምቾት አልባ አድርጎታል፡፡ ይሁን እና በትምህርት ቤቱ ቅጥር ግቢ የተገነቡት ክፍሎች የክፍል ጥበቱን በተወሰነ ደረጃ መቀነስ ስለሚያስችሉ ለመማር ማስተማሩ አዎንታዊ ሚና ይጫወታሉ ብሏል፡፡
የወተት በር አጠቃላይ አንደኛ ደረጃ ትምህርት ቤት መምህርት አስናቀች አስማረ በክፍል ጥበት ምክንያት በአንድ ጠረጴዛ አራት ተማሪዎች ተጨናንቀው ስለሚቀመጡ ለመከታተል፣ ለመቆተጣጠር እና ለመመዘን አስቸጋሪ ነው ብለዋል፡፡ ስለኾነም የክፍል ግንባታው ተማሪዎች ዘና ብለው እንዲማሩ ስለሚያደርግ ጠቀሜታው ከፍተኛ እንደኾነ ተናግረዋል፡፡
የጠይማ አጠቃላይ አንደኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ርእሰ መምህር ሙሉጌታ ባለው እንዳሉት “ኬር ኢትዮጵያ” ክፍል ገንብቶ አስረክቦናል፤ የጓሮ አትክል በሠርቶ ማሳያ አልምቶ በመስጠቱም ትምህርት ቤቱን ዘርፈ ብዙ ተጠቃሚ እንዳደረገው አውስተዋል፡፡ የ”ኬር ኢትዮጵያ” የአማራ ክልል አስተባባሪ ጎበዜ አያሌው በባሕር ዳር ከተማ የሚገኙ ትምህርት ቤቶችን ተመልክተው እና በጥናት ችግሮቻቸውን በመለየት ወደ ሥራ መግባታቸውን አስረድተዋል፡፡
40 ሚሊዮን ብር ወጭ በማድረግም በ11 ትምህርት ቤቶች የመማሪያ፣ የመጸዳጃ፣ የልጃገረዶች የንጽህና መጠበቂያ ክፍሎች እንዲሁም ንጹህ የመጠጥ ውኃ እና ዘመናዊ የቆሻሻ ማቃጠያ ግንባታዎችን በአዲስ እንዲሁም የአንድ ትምህርት ቤትን እድሳት በማጠናቀቅ ማስረከባቸውን ተናግረዋል፡፡
ግንባታዎችም ተማሪ ተኮር የተለያዩ የአገልግሎት መስጫ መኾናቸውን ነው ያብራሩት፡፡ አስተባባሪው አክለውም ነባር የተለያዩ ክፍሎችን በማደስ መማር ማስተማሩ በጥራት እንዲከናወን እያገዙ እንደሚገኙ ጠቁመዋል፡፡
ግንባታዎቹ 22 ሺህ ተማሪዎች ትምህርታቸውን በአግባቡ እና በምቾት እንዲከታተሉ ያደርጋቸዋልም ብለዋል፡፡
የባሕር ዳር ከተማ አሥተዳደር ትምህርት መምሪያ ኀላፊ ሙሉዓለም አቤ (ዶ.ር) እንዳሉት ኬር ኢትዮጵያ በባሕር ዳር ከተማ በ10 አጠቃላይ የአንደኛ ደረጃ እና በሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች ደረጃውን የጠበቀ ትምህርት መስጠት የሚያስችሉ ግንባታዎችን አጠናቅቆ አስረክቦናልም ብለዋል፡፡ በተጨማሪም የጓሮ አትክልት አልምቶ ርክክብ አድርገናል ነው ያሉት፡፡
እነዚህ የተማሪ ተኮር የአገልግሎት መስጫ ግንባታዎች የተማሪን ተሳትፎ በማሳደግ የትምህርትን ጥራት ያመጣሉ ያሉት ዶክተር ሙሉዓለም የልዩ ፍላጎት ተማሪዎችን ችግርም መቅረፍ ያስችላሉ ብለዋል፡፡
ተማሪዎች አዘውትረው ወደ ትምህርት ቤት እንዲመጡ ብሎም በቆይታቸው ደስተኛ እንዲኾኑ እንደሚያስችላቸው መምሪያ ኀላፊው አብራርተዋል፡፡
ሌሎች ረጅ ድርጅቶችም የኬር ኢትዮጵያ ፈለግን ሊከተሉ እንደሚገባም ጠቁመዋል፡፡
ዘጋቢ፦ ሙሉጌታ ሙጨ
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን