
ባሕር ዳር: ሚያዝያ 30/2017 ዓ.ም (አሚኮ) አዋጅ ቁጥር 1156/2011 ስለ አሠሪ እና ሠራተኛ ደኅንነት፣ ጤንነት፣ ስለ ሠራተኛ መብት እና ግዴታ፣ ስለ አሠሪ መብት እና ኀላፊነት በአጠቃላይ በአሠሪው እና በሠራተኛው መካከል መኖር ስላለበት የሥራ መስተጋብር ዙሪያ የሚያትት የሕግ ድንጋጌ ነው።
በሀገሪቱ ታሪክ እንደየዘመኑ የሥራ ባህሪ እና የእድገት ሁኔታ የአሠሪ እና ሠራተኛ መብት እና ግዴታን አስመልክቶ የተለያዩ አዋጆች እየወጡ ከጊዜ በኋላ በተለያዩ ምክንያቶች በሌላ አዋጅ እየተተኩ እንደቆየ ታሪክ ያስረዳል። አዲሱ የአሠሪ እና ሠራተኛ ጉዳይም አዋጅ ቁጥር 1156/2011 ተብሎ ከዚህ ቀደም የነበረውን አዋጅ ከነ ማሻሻያዎቹ በመሻር እና የግል ሥራ እና ሠራተኛ አገናኝ ኤጀንሲ አዋጅ ቁጥር 632/2001ን በአዲሱ አዋጅ ውስጥ በማካተት ነው በሥራ ላይ የዋለው፡፡
አቶ አጥናፍ በላይ በአማራ ክልል አሠሪ እና ሠራተኛ ጉዳይ ባለሥልጣን የኢንዱስትሪ ግንኙነት ዳይሬክተር ናቸው። ባለሥልጣኑ ዋና ሥራው በሕዝቦች ዘንድ አዋጆችን እና ደንቦችን አውቆ በመንቀሳቀስ ረገድ መሠረታዊ ክፍተት ያለ በመኾኑ ሕጉን ማሳወቅ ትልቁ ሥራችን ነው ይላሉ። ምክንያቱም ሕግን ካለማወቅ የሚከሰቱ መሠረታዊ ክፍተቶች ከተጠያቂነት አያድኑምና ብለዋል።
በሥራ ቦታ ውስጥ የአሠሪዎች፣ የሠራተኞች እና የመንግሥት ኀላፊነት መኖር እንዳለበት አዋጅ ቁጥር 1156/2011 በግልጽ እንዳስቀመጠ ገልጸዋል። ሠራተኞች በሥራ ወቅት የሚያደርጉት ጥንቃቄ አለ፤ አሠሪዎችም ሠራተኞች በሥራ ምክንያት አደጋ እና ጫና እንዳይደርስባቸው፣ በጤንነታቸው እና በደኅንነታቸው ላይ ጉዳት እንዳይከሰትባቸው የመጠበቅ ኀላፊነት እንዳለባቸው አዋጁ ይደነግጋል ነው ያሉት።
የአሠሪ እና ሠራተኛ ጉዳይ ባለሥልጣን ደግሞ እንደ ተቋም ሕጎቹን በተገቢው መንገድ የማስፈጸም ኀላፊነት አለበት ብለዋል። አዋጁ በእውኑ ሥራ ላይ እየዋለ ነው ወይ? ብሎ የመከታተል እና የማሳወቅ ኀላፊነት እንዳለበትም ተናግረዋል። ችግሮች ካሉም ተከታትሎ እርማት እና ማስተካከያ የማሰጠት ኀላፊነት አለበት ነው ያሉት።
በአዋጁ ከአንቀጽ 92 እስከ 113 አሠሪም ኾነ ሠራተኛ ግዴታዎች እና መብቶች እንዳሉባቸው በግልጽ የተቀመጠ ነው ብለዋል። በአንጻሩ በመሥራት እና በማሠራት ወቅት ሕገ ወጥ ድርጊትን በግልጽ የለየ አዋጅ ነው ይላሉ። የአሠሪ ግዴታዎች ብሎ ካስቀመጣቸው ውስጥ ሠራተኛው በሥራ ቦታ አደጋ ሳይደርስበት እንዲሠራ የማድረግ ጥቅል ግዴታ እንዳለበት ገልጸዋል። ይህም ሲባል የሥራ ቦታውን አደገኛነት በመለየት የሚያቀርባቸው የደኅንነት መጠበቂያ መንገዶች መኖር እንዳለበት ሕጉ ያዝዛል ነው ያሉት።
የአደጋ ጊዜ መከላከያ መሣሪያዎችን አሠሪ ማቅረብ እንዳለበት ሕጉ አስቀምጧል ብለዋል። ከዚያ በፊት ግን በሠራተኛው ደኅንነት ላይ አደጋ ሊጥሉ የሚችሉ ነገሮችን ማስወገድ አለበትም ነው ያሉት። ደኅንነትን እና ጤንነትን የሚያጓድሉ ነገሮች ሁሉ አሠሪውን ያገበዋልና ቀድሞ መፍትሔ ማበጀት ይኖርበታል ብለዋል።
ለምሳሌ ይላሉ ዳይሬክተሩ ሠራተኛው እየሠራው ያለው ሥራ ለብዙ ሰዓት የሚያቆይ እና አስቸጋሪ ከኾነ እረፍት እየሰጠ ማሠራት እንዳለበትም ሕጉ ያዝዛል ነው ያሉት። ይህም አዋጭ ካልኾነ ለመሥራት አስቸጋሪ የኾነውን ነገር የሚከላከልበት የሥራ መሣሪያ ማሟላት ይኖርበታል ብለዋል።
በአዋጁ አንቀጽ 92 ላይ የአሠሪ ግዴታ ብሎ በግልጽ ካስቀመጣቸው ውስጥ የሙያ ደኅንነት እና ጤንነትን ሊያጓድሉ የሚችሉ ነገሮችን የመከላከል ግዴታ እንዳለበት ተደንግጓል ነው ያሉት። አደጋ ተከላካይ ሠራተኞችን የመመደብ እና የሙያ ደኅንነት እና ጤንነት ኮሚቴ ማቋቋም እንዳለበትም አዋጁ ይገልጻል ብለዋል።
የአደጋ መከላከያ መሣሪያዎችን የማቅረብ ግዴታ አለበት። ስለ መሣሪያው አጠቃቀምም ሥልጠና መስጠት የአሠሪው ግዴታ ነው ብለዋል። በሥራ ቦታ ሊከሰቱ የሚችሉ በሽታዎችን እና አደጋዎችን ለሚመለከተው አካል የማሳወቅ ኀላፊነትም አለበት ነው ያሉት። አዲስ ለሚቀጠሩ ሠራተኞች ስለ አደገኛነቱ እና አጠቃላይ ስለ አሠራሩ ቀድሞ ትምህርት የመስጠት ኀላፊነት እንዳለበትም በአዋጁ ተቀምጧል ብለዋል።
በሕገ መንግሥቱም ሠራተኞች ጤናማ በኾነ የሥራ አካባቢ የመሥራት መብት እንዳላቸው በአጽንኦት እንደተቀመጠ ዳይሬክተሩ ገልጸዋል። ከአቅም በላይ መሥራት፣ ለረጅም ጊዜ ቆሞ መሥራት፣ ለረጅም ጊዜ አጎንብሶ መሥራት፣ ለረጅም ጊዜ ተቀምጦ መሥራት ብቻ ከጊዜ በኋላ ለጉዳት የሚዳርጉ የአሠራር ዘይቤዎችንም ግምት ውስጥ ማስቀመጥ እንደሚገባ በአዋጁ የተገለጸ ነው ብለዋል።
ለምሳሌ አጭር የኾነ ሠራተኛ ሁልጊዜ እየተንጠራራ የሚሠራ ከኾነ በአካሉ ላይ አንድ ቀን ችግር ይፈጥራል ነው ያሉት። በአንጻሩ ደግም ረጅም የኾነ ሰው ሁልጊዜ አጎንብሶ ከሠራም እንዲሁ በሰውነቱ ላይ ችግር ሊፈጠር ይችላል ብለዋል። አዋጁ ለዚህ ሁሉ ግምት ውስጥ ማስገባት እንደሚያስፈልግ ያነሳል ነው ያሉት።
በአንጻሩ ሠራተኛውም ቢኾን ግዴታ እና ኀላፊነት እንዳለበት በሕጉ የተቀመጠ ነው ብለዋል። የተሠጠውን መመሪያ እና ደንብ አክብሮ የሚሠራ መኾን እንዳለበት አስቀምጧል ይላሉ። የአደጋ መከላከያ ተብለው የተሰጡ ቁሳቁሶችን በአግባቡ የመጠቀም ኀላፊነት አለበት ነው ያሉት። የተቀመጠውን የሥራ መሣሪያ ቢሸጥ ሕገ ወጥ ነው ብለዋል። በሥራ ወቅት አደጋ የሚያደርስን ነገር ለአሠሪው አካል የማሳወቅ ኀላፊነትም አለበት ብለዋል።
የተቀመጠውን አዋጅ ባንድም ኾነ በሌላ መንገድ ጥሶ የተገኘ አሠሪም ኾነ ሠራተኛ እንደፈጸመው ጥፋት ስፋት እና ጥልቀት ታይቶ ከገንዘብ መቀጫ እስከ በወንጀል ሕግ መጠየቅ ድረስ ሊያስቀጣ እንደሚችል በሕጉ ተመላክቷል። አዋጁን ተግባራዊ በማድረግ ረገድ በአሠሪውም ኾነ በሠራተኛው ላይ ክፍተት እንዳለ ዳይሬክተሩ ተናግረዋል። እንደ ክልልም አዋጁን ጥሰው በተገኙ አካላት ላይ የተወሰዱ እርምጃዎች ያሉ ቢኾንም እንኳ በቀጣይ ሰፊ ጥረትን የሚጠይቅ ነው ብለዋል። የግንዛቤ እጥረትም አንዱ ፈተና እንደኾነ ገልጸዋል።
በአጠቃላይ ጤናማ ሥራን ከጤናማ ሠራተኛ ጋር ለማዋሐድ በሚደረገው ጥረት አዋጁ በግልጽ እንዳስቀመጠ መገንዘብ ይቻላል። ከሥራ ይልቅ የሰው ደኅንነት መቅደም እንዳለበትም ዳይሬክተሩ በአጽንኦት አንስተዋል። የተቀመጠውን አዋጅ በሚገባ ባለመጠቀም ምክንያት በአሠሪ እና በሠራተኛው ላይ የሚስተዋሉ የጤንነት እና የደኅንነት ችግር አሁንም ይስተዋላል። መመሪያዎች እና ደንቦች በተግባር መተርጎም አለባቸው።
የዘንድሮው የሠራተኞች ቀን በዓለም ለ136ኛ፣ በሀገራችን ደግሞ ለ50ኛ ጊዜ ታስቦ ውሏል።
ዘጋቢ:- ሰለሞን አንዳርጌ
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን