
ባሕር ዳር:ሚያዚያ: 30/2017 ዓ.ም (አሚኮ) የአንድ ማዕከል አገልግሎት ቴክኖሎጂ የተለያዩ የመንግሥት ወይም የግል ተቋማት አገልግሎቶችን በአንድ ዲጂታል ሥርዓት በማቀናጀት ደንበኞች የተለያዩ አገልግሎቶችን በአንድ ቦታ እንዲያገኙ ማድረግ የሚያስችል የቴክኖሎጂዎች ትስስር ነው።
ቴክኖሎጂው የአሥተዳደር ሂደቶችን ለማቀላጠፍ፣ ተደራሽነትን ከፍ ለማድረግ እና የደንበኞችን እርካታ ለማሳደግ የላቀ አስተዋፅዖ ያደርጋል።
በአንድ ማዕከል ተቀናጅቶ ሕይዎትን ቀለል የሚያደርገው ቴክኖሎጂ የመንጃ ፍቃድ፣ የዲጂታል መታወቂያ፣ የባንክ አገልግሎት፣ የኢሚግሬሽን እና የዜጎች አገልግሎት እንዲሁም የዲጂታል የክፍያ አማራጮችን በአንድ ጥላ ስር ማቅረብ ያስችላል።
ዲጂታላይዜሽንን በማፋጠን ዜጎች መንግሥት በሚያቀርብላቸው አገልግሎቶች እርካታን እንዲያገኙ፣ ጊዜን፣ ሃብትን እና ጉልበትን እንዲቆጥቡ ይረዳል፡፡
በቅርቡ በጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ.ር) የተመረቀው እና የዲጂታል ኢትዮጵያ ስኬት መገለጫ የኾነው መሶብ የአንድ ማዕከል አገልግሎት የዚህ ማሳያ ነው፡፡
በመሶብ የተለያዩ የመንግሥት አገልግሎቶች በዲጂታል ቴክኖሎጂ ተሳስረው የሚቀርቡበት በመኾኑ ዜጎች የተሟላ የዲጂታል አማራጮችን በመጠቀም በቀላሉ አገልግሎቶችን ማግኘት የሚያስችላቸው መኾኑም በማዕከሉ ምረቃ ወቅት ተጠቁሟል።
በመሶብ የአንድ ማዕከል አገልግሎት 12 ተቋማት በአንድ የተሳሰሩበት እና ከ40 በላይ አገልግሎቶች የሚገኝበትም ነው፡፡
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!