
ባሕር ዳር:ሚያዝያ 30/2017 ዓ.ም (አሚኮ) የአማራ ክልል ባሕል እና ቱሪዝም ቢሮ ቅርሶችን በራስ አቅም መጠገን የሚያስችል የባሕላዊ ኖራ ማቀነባበሪያ ፋብሪካ በምዕራብ በለሳ ሊገነባ ነው። ቢሮው የፋብሪካውን ግንባታ አስመልክቶ ከአካባቢው ማኅበረሰብ እና ባለድርሻ አካላት ጋር እየተወያየ ነው።
የአማራ ክልል ባሕል እና ቱሪዝም ቢሮ ኀላፊ መልካሙ ፀጋዬ እንዳሉት የኖራ ፋብሪካው እምቅ የኖራ ሃብት ባለበት የማዕከላዊ ጎንደር ዞን በለሳ ወረዳ ላይ የሚገነባ ነው።
በቅርስ ጥገና ወቅት ዋነኛውን ዋጋ የሚወስደው የኖራ ወጭ ነው፤ የሚገነባው የኖራ ማቀነባበሪያ ፋብሪካ ወጪ እና የቅርሶችን ታሪካዊ ይዘት ጠብቆ ለማደስ ያስችላል ነው ያሉት። በአማራ ክልል ከፍተኛ የኾነ የኖራ ማዕድን ክምችት ቢኖርም ቅርሶችን ለመጠገን ይውል የነበረው የተቃጠለ ኖራ ከአማራ ክልል ውጭ ይመጣ እንደ ነበር ተናግረዋል። ይህም ከፍተኛ የኾነ የትራንስፖርት ወጭን አስከትሎ ቆይቷል።
“ጥንት አባቶቻችን ቅርሶችን የሠሩት ኖራን በባሕላዊ መንገድ እያቃጠሉ ነበር፤ አሁንም የአባቶቻችንን የቅርስ ሥራ ጥበብ ከአሁኑ ትውልድ ጋር የሚያስተሳስር ፋብሪካ ልንተክል ነው” ሲሉም ተናግረዋል። ፋብሪካውን የሚገነባው ተቋራጭ ተለይቷል፤ ግንባታው የሚያርፍበት እና የጥሬ እቃ ማውጫ ቦታውም ተለይቶ ተይዟል ነው ያሉት ቢሮ ኀላፊው።
ቢሮው የመጀመሪያውን የባሕላዊ ኖራ ማቀነባበሪያ ፋብሪካ በምዕራብ በለሳ ይጀምር እንጂ በቀጣይነትም በሌሎች አካባቢዎች ተጨማሪ ፋብሪካዎች ይገነባሉ ብለዋል። ደረጃውን የጠበቀ እና በቂ ኖራ ማምረት ቅርሶችን ከጥፋት የመታደግ ጉዳይ መኾኑን በውል ተገንዝበን እየሠራን ነው ሲሉም ተናግረዋል።
በመርሐ ግብሩ ላይ የተገኙት የማዕከላዊ ጎንደር ዞን ዋና አሥተዳዳሪ አወቀ አስፈሬ ዞኑ በርካታ እና እድሜ ጠገብ የቅርስ ሃብቶች ያሉት መኾኑን ተናግረዋል። የአጼ ፋሲል አብያተ መንግሥታትን ጨምሮ በዞኑ በመፍረስ ላይ የነበሩ ቅርሶችን የመጠገን ሥራ በትኩረት እየተሠራ ስለመኾኑም አንስተዋል።
በምዕራብ በለሳ የሚገነባው ባሕላዊ የኖራ ማቀነባበሪያ ፋብሪካ ለተያዘው ቅርሶችን ጠግኖ ለትውልድ የማስተላለፍ ሥራ ዋነኛ አጋዥ እንደሚኾንም ጠቁመዋል።
የክልሉ ባሕል እና ቱሪዝም ቢሮ አካባቢውን ለዚህ ፋብሪካ በጥናት መርጦ በመምጣቱ አመስግነው የዞኑ አሥተዳደርም ከአካባቢው ሕዝብ ጋር በጋራ በመኾን ችግሮችን ሁሉ እየፈታ ፋብሪካው ከዳር እንዲደርስ ይሠራል ብለዋል አቶ አወቀ።
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን