በተለያዩ የሥራ ዘርፎች በመሠማራት ተጠቃሚ መኾናቸውን የአዊ ብሔረሰብ አሥተዳደር ወጣቶች ተናገሩ።

9

ባሕር ዳር፡ ሚያዝያ 30/2017 ዓ.ም (አሚኮ) የአዊ ብሔረሰብ አሥተዳደር ወጣቶችን በተለያዩ የሥራ ዘርፎች በማሠማራት ተጠቃሚ ለማድረግ እየተሠራ ነው። በተለይ ወጣቶችን በእንስሳት ማድለብ እና ወተት ልማት፣ በዶሮ እርባታ እና በሰብል ልማት፣ በማኒፋክቸሪንግ እና አግልግሎት ዘርፍ በአጭር ጊዜ ውጤታማ እንዲኾኑ ከተማ አሥተዳደሩ ትኩረት ሰጥቶ እየሠራ መኾኑን ነው የገለጸው።

በብሔረሰብ አሥተዳደሩም በርካታ ወጣቶች በተሠማሩባቸው የሥራ መስክ ለወጥ እያሥመዘገቡ ካሉባቸው ወረዳዎች እና ቀበሌዎች የጓንጓ ወረዳ ስጋዲ ቀበሌ ተጠቃሽ ነው። በስጋዲ ቀበሌ እንስሳትን በማድለብ ከተሠማሩ ወጣቶች መካከል ወጣት ሰለሞን አበጀሁ የጓንጓ ወረዳ ወጣቶችን ሲያደራጅ በዕድሉ ተጠቅሞ ወደ ሥራ መግባት መቻሉን ነው ለአሚኮ የተናገረው።

ወጣት ሰለሞን ከአራት ወጣቶች ጋር በመኾን በ200 ሺህ ብር መነሻ ካፒታል “ሰለሞን፣ ቸኮል እና ጓደኞቹ የሽርክና ማኅበር” በሚል ስያሜ ወደ ሥራ መግባታቸውን ገልጿል። ወጣት ሰለሞን ተደራጅተው ወደ እንስሳት ማድለብ ሥራ ከተሠማሩ በኋላ ውጤታማ እና ተጠቃሚ መኾናቸውን ገልጿል።

በሀገር እና ክልል ደረጃ የተፈጠረው የጸጥታ ችግር ሥራቸውን ቢፈትነውም ለፈተና ሳይበገሩ ሥራውን ማስቀጠላቸውን ተናግሯል። በአሁኑ ወቅትም ቤተሠብ ከመመሥረት ጀምሮ ከተማ ሁለት ቤት መግዛት መቻሉን ወጣቱ ተናግሯል። ገንዘብ በመቆጠብ የተሻለ ኑሮ እየመሩ ስለመኾኑም አብራርቷል።

ወጣቶችም ለሥራው ትኩረት በመስጠት ከሠሩ ይለወጣሉ ያለው ወጣት ሰለሞን ወጣቶች ቶሎ ተስፋ መቁረጥ አይገባቸውም ብሏል። ወጣት አብዱ ዘይኑ ቻግኒ ከተማ ውስጥ የአንድ ቀን ጫጩት ተረክቦ የሥጋ ዶሮዎችን በማሠደግ ሥራ ላይ የተሠማራ ሌላኛው ወጣት ነው። ሥራ ከጀመረ ጥቂት ጊዜ ቢኾንም አሁን ላይ በኑሮው ለወጥ ማምጣቱን ይናገራል።

ከተማ አሥተዳደሩ በሥልጠና እና በሥራ ዕድል ምቹ ሁኔታ ከመፍጠር በተጨማሪ ባለሙያዎች በየጊዜው ሙያዊ ድጋፍ እያደረጉላቸው መኾኑንም ገልጿል። ለቀጣይ ሥራውን በማሥፋት ለከተማዋ ወጣቶች ሞዴል ለመኾን አቅደው እየሠሩ መኾንም ተናግሯል። በአዊ ብሔረሰብ አሥተዳደር የጓንጓ ወረዳ ሥራ እና ሥልጠና ጽሕፈት ቤት ኀላፊ እሱባለው ይሁን በወረዳ ደረጃ በበጀት ዓመቱ 6 ሺህ 183 ወጣቶች መመዝግባቸውን ገልጸዋል።

እነዚህ የተመዘገቡ ወጣቶችን በግብርና፣ በማዕድን፣ በአገልግሎት ዘርፍ፣ በማኑፋክቸሪንግ ዘርፍ እና በሌሎች የመንግሥት ፕሮጀክቶች 4 ሺህ 566 ወጣቶች ተሠማርተዋል ነው ያሉት። የብድር አቅርቦት እና ሌሎች የመሠረተ ልማት ጥያቄዎችን ያለምንም ቢሮክራሲ እንዲፈታላቸው፣ የብድር ዋስትናም በቤት ካርታ እና በደሞዝ ብቻ ሳይኾን በመሬት አረንጓዴ ደብተር እንዲመቻችላቸው ጉዳዩ ከሚመለከታቸው ተቋማት ጋር ውውይት እየተደረገ ነው ብለዋል።

ሁሉም ተቋማት ለወጣቶች የሥራ ዕድል እንዲፈጥሩ ውይይት ተደርጎ ወደ ሥራ መግባታቸውንም አቶ እሱባለው ገልጸዋል። የአዊ ብሔረሰብ አሥተዳደር ሥራ እና ሥልጠና መምሪያ ኀላፊ ታፈረ ከበደ በአሥተዳደሩ በ2017 በጀት ዓመት ለ70 ሺህ 839 በላይ ሥራ ፈላጊ ወጣቶች የሥራ ዕድል ለመፍጠር ታቅዶ ወደ ሥራ ስለመገባቱ ነው የተናገሩት።

ለወጣቶቹ በሦስት የሥራ ዘርፎች የሥራ ዕድል ተፈጥሯል ነው ያሉት። በተለይ በግብርና፣ በማኑፋክቸሪንግ፣ በኢንዱስትሪ እና በአግልግሎት ዘርፎች ወጣቶች እንዲሠማሩ መደረጉንም ነው ያብራሩት። ይህ ዘገባ እስከተጠናቀረበት ጊዜ ድረስ 34 ሺህ 711 ሥራ ፈላጊ ወጣቶች የሥራ ዕድል ተፈጥሮላቸዋል ነው ያሉት ኀላፊው።

የብድር አቅርቦት እና የመሠረተ ልማት ጥያቄዎች አፋጣኝ ምላሽ እንዲያገኙም እየተሠራ መኾኑን ገልጸዋል። የብድር አቅርቦትን በዘላቂነት ለመፍታት ለወጣቶች የተሠጠውን ተዘዋዋሪ ብድር በአግባቡ ለማስመለስ የጸጥታ ችግሩ ፈተና መኾኑን አብራርተዋል። እስከ አሁን 8 ቢሊዮን ብር ከተሠጠው ብድር ውስጥ 28 ሚሊዮን ብር ብቻ ማስመለስ መቻሉን አንስተዋል። በቀጣይ የተሠጠውን ተዘዋዋሪ ብድር ለማስመለስ ሁሉም አካል መረባረብ እንደሚገባውም መምሪያ ኀላፊው አሳስበዋል።

ዘጋቢ፦ሰሎሞን ስንታየሁ

የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን

Previous articleፕሬዝዳንት ታዬ አፅቀሥላሴ በ80ኛው የሩሲያ የድል በዓል ላይ ለመታደም ሞስኮ ገቡ።
Next article“መርሐችን የጀመርነውን የልማት ሥራ አጠናቅቀን ሪቫን መቁረጥ ነው” አብዱ ሁሴን (ዶ.ር)