
ባሕር ዳር: ሚያዚያ: 30/2017 ዓ.ም (አሚኮ) የኢፌዴሪ ፕሬዝዳንት ታዬ አፅቀሥላሴ ነገ በሚከበረው 80ኛው የሩሲያ የድል በዓል ላይ ለመታደም ዛሬ ማለዳ ሞስኮ ገብተዋል። የሁለተኛው የዓለም ጦርነት ማብቃቱን ተከትሎ በተለይም ደግሞ የቀድሞው ሶቪየት ኅብረት በናዚ ጀርመን ላይ የተቀዳጀውን ድል በማሰብ ነገ በሩሲያ መዲና ሞስኮ ለ80ኛ ጊዜ ለሚከበረው በዓል በርካታ ቁጥር ያላቸው የዓለም መሪዎች ይታደማሉ ተብሎ ይጠበቃል።
ኢዜአ ከስፍራው እንደዘገበው የበርካታ አፍሪካ ሀገራት መሪዎች የቻይና እና የብራዚል ፕሬዝዳንቶችን ጨምሮ በዚሁ የድል በዓል ላይ ይሳተፋሉ። ከ80ኛው የሩሲያ የድል በዓል ተሳትፎ ጎን ለጎን ፕሬዝዳንት ታዬ አፅቀሥላሴ ከተለያዩ አካላት ጋር የሁለትዮሽ እንዲሁም ባለብዙ ወገን ዲፕሎማሲያዊ ውይይቶችን ያደርጋሉ ተብሎም ይጠበቃል።
በአሁኑ ወቅት በኢትዮጵያ እና በሩሲያ መካከል ያለው ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነት በተለያዩ ዘርፎች እየጎለበተ መምጣቱን በበቂ ሁኔታ መረጃዎች ያመላክታሉ። ሁለቱ ሀገራት በጤና ትብብር፣ በኢኮኖሚያዊ፣ ዲፕሎማሲ፣ በንግድ፣ በኢንቨስትመንት እና በቴክኖሎጂ ዘርፎች ያላቸውን ግንኙነት ከጊዜ ወደ ጊዜ እያሳደጉ ነው። ይህም በቅርብ ጊዜ በተደረጉ ስምምነቶችና ውይይቶች በርካታ የመግባቢያ ሰነዶች ስምምነት ላይ መደረሱ የሚታወስ ነው።
ለአብነትም በተያዘው ዓመት ሕዳር ወር 2017 ዓ.ም መጀመሪያ ላይ “ሩሲያ እና ኢትዮጵያ ለትበብር ጊዜ አይጠብቁም” በሚል መሪ ቃል በአዲስ አበባ የተካሄደው የሁለቱ ሀገራት የቢዝነስ ፎረም የሀገራቱ ባለስልጣናት፣ የንግድ ማኅበረሰብ እና ኢንቨስተሮችን ያሳተፈ እንደነበረም ይታወሳል።
ፕሬዝዳንት ታዬ ሞስኮ ሲደርሱ በሩሲያ ፌዴሬሽን የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ከፍተኛ ባለስልጣን አናቶሊ ባሽኪን አቀባበል አድርገውላቸዋል።
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!