
የኅብረተሰብ ጤና ኢንስቲቲዩት በበኩሉ የክልሉ የአጎበር ስርጭት መቶ በመቶ እንደሆነና አጠቃቀሙ 80 በመቶ መድረሱን አስታውቋል።
ባሕር ዳር፡ ግንቦት 12/2012 ዓ.ም (አብመድ) በዚህ ወቅት ስለወባ ግንዛቤ ከመፍጠር ባለፈ ግብዓት እየቀረበ እንዳልሆነ በምዕራብ ጎንደር ዞን ምዕራብ አርማጭሆ ወረዳ በስልክ ያነጋገርናች ነዋሪዎች ገለጹ። ነዋሪዎች እንደገለጹት አጎበር የሚቀርበው በየሦስት ዓመቱ በመሆኑ ወደ አካባቢው የሚገቡ አዳዲስ ነዋሪዎች በቀላሉ ማግኘት አልቻሉም። ችግሩ ተከስቶ በማኅበረሰቡ ላይ ጉዳት ከማድረሱ በፊት መንግሥት አስፈላጊ ግብዓቶችን እንዲያቀርብ እና የመከላከል ሥራው ላይ እንዲሠራም ጠይቀዋል።
የምዕራብ አርማጭሆ ወረዳ ጤና ጥበቃ ጽሕፈት ቤት ምክትል ኃላፊ ደሳለኝ አስራት እንደገለጹት ለነዋሪዎች የንጽሕ አጠባበቅና እና የአጎበር አጠቃቀም ግንዛቤ ፈጠራ ላይ እየተሠራ ነው። የኬሚካል መርጫ መሣሪያዎችንም የመለየት እና የመሰብሰብ ሥራ እየተሠራ እንደሚገኝ ገልጸዋል። ይሁን እንጂ እስካሁን በክልል በኩል የቀረበ ግብዓት አለመኖሩ ተናግረዋል። አጎበሩ በየሦስት ዓመት ስለሚሰራጭ በእነዚህ ዓመታት ውስጥ ወደ ወረዳው በነዋሪነት የሚመጡ ሰዎች አጎበር በቀላሉ እንደማያገኙም ኃላፊው ነግረውናል።
የምዕራብ ጎንደር ዞን ማኅበራዊ ልማት መምሪያ ኃላፊ ክሽን ወልዴ እንደገለጹት ደግሞ አካባቢው ለሱዳን ካለው ቅርበትና ተጋላጭነት አንጻር የኮሮና ወረርሽኝን መከላከል ላይ ትኩረት ተደርጎ ቆይቷል። ይሁን እንጂ ወቅቱ የክረምት መግቢያ በመሆኑና አካባቢው ወባ የሚከሰትበት በመሆኑ መከላከልን መሠረት ያደረገ ሥራ እየተከናወነም እንደሆነ ገልጸዋል፡፡ በዚህ ወቅትም በአጎበር አጠቃቀም እና ለወባ ትንኝ መራቢያ ምቹ የሆኑ ቦታዎችን የማፋሰስና የማዳፈን ተግባር ዙሪያ የግንዛቤ ፈጠራ እየተሠራ እንደሚገኝ ወይዘሮ ክሽን ገልጸዋል።
ዞኑ የልማት ቀጣና ከመሆኑ ጋር ተያይዞ ወደ አካባቢው ከፍተኛ ቁጥር ያለው ሠራተኛ ስለሚገባ ይህንን ታሳቢ ያደረገ አጎበር እና ኬሚካል እንዲቀርብላቸው እንዲሁም በክልሉ በኩል የሚቀጠሩ የኮንትራት ሠራተኞች በወቅቱ እንዲላኩላቸው ጠይቀዋል። ይሁን እንጂ እስከ ግንቦት 06/2012ዓ.ም ድረስ ወባን ለመከላከል የሚያስፈልጉ ግብዓቶች አለመቅረባቸውን ወይዘሮ ክሽን ገልጸዋል።
የአማራ ክልል ኅብረተሰብ ጤና ኢንስቲቲዩት የወባ ፕሮግራም አስተባባሪ ወይዘሮ ማስተዋል ወርቁ እንደገለጹት በዚህ ወቅት የዓለም ጤና ድርጅት ከኮሮና ውጭ ትኩረት የሚሹ ብሎ በለያቸው 23 በሽታዎች ላይ በትኩረት እየተሠራ ይገኛል።
ከእነዚህ በሽታዎች ውስጥ ወባ አንዱ እንደሆነ የገለጹት ወይዘሮ ማስተዋል በጤና ተቋማት የተላኩ መረጃዎችን መሠረት በማድረግ ስርጭቱ በጨመረባቸው ወረዳዎች ለማኅበረሰቡ የግንዛቤ ፈጠራ እየተሠራ መሆኑን ገልጸዋል።
ወይዘሮ ማስተዋል አንደገለጹት ከሚያዝያ እስከ ሰኔ እና ከመስከረም እስከ ታኅሣስ ባለው ጊዜ ወባ የሚከሰትበት ወቅት በመሆኑ የመከላከል ሥራዎች ላይ በትኩረት እየተሠራ ይገኛል።
ምንም እንኳን የአጎበር ችግር እንዳለ ያነጋገርናቸው ነዋሪዎች እና ኃላፊዎች ቢገልጹም የክልሉ የአጎበር ስርጭት መቶ በመቶ እንደሆነ እና አጠቃቀሙ 80 በመቶ መሆኑን ባለሙያዋ አስታውቀዋል።
ከአምስት ዓመታት በፊት በክልሉ በርካታ የወባ ሕሙማን ሪፖርት ይደረግ እንደነበር የገለጹት አስተባባሪዋ ከአምስት ዓመታት ወዲህ ግን የሕሙማን ቁጥር መቀነሱን ገልጸዋል። ከ2010 ዓ. ም ጀምሮ ደግሞ ቁጥሩ መጨመሩን ባለሙያዋ ነግረውናል።
በምዕራብ ጎንደር ዞን ቋራ፣ መተማ እና ምዕራብ አርማጭሆ ደግሞ ከፍተኛ የወባ ስርጭት የሚታይባቸው ወረዳዎች መሆናቸው ተገልጧል።
በባሕር ዳር ከተማ አስተዳድር ደግሞ በ2011 ዓ.ም በ2010 ዓ.ም ከነበረው በ300 እጥፍ መጨመሩን ባለሙያዋ ገልጸዋል። በአካባቢው ከሚገኙ ሕሙማን ባለፈ ከሌሎች አካባቢዎች በሪፈር የሚመጡ ሕሙማን መኖር ለቁጥሩ መጨመር በምክንያትነት ቢጠቀስም በጭስ ዓባይ አካባቢ ስርጭቱ ይበልጥ መጨመሩን ነው ባለሙያዋ የነገሩን።
የኅብረተሰቡ መዘናጋት፣ አጎበርን በአግባቡ ያለመጠቀም፣ የአካባቢ ቁጥጥር ሥራ ዝቅተኛ መሆን በክልሉ ለወባ መጨመር በምክንያትነት ተቀምጠዋል። ችግሩንም ለመፍታት መድረኮች ተፈጥረዋል፤ ባለሙያዎችም የግንዛቤ ማስጨበጫ ሥራዎችን በመሥራት ላይ ይገኛሉ። የአጎበር አጠቃቀም ክትትል ሥራም እየተሠራ ይገኛል።
በባሕር ዳር አካባቢ ደግሞ ከእነዚህ መፍትሔዎች በተጨማሪ ፈጣን የቤት ለቤት ምርመራና ሕክምና፣ ትኩሳት የተሰማው ማንኛውም ሰው በ24 ሰዓት ውስጥ በጤና ተቋማት ምርመራ እንዲያደርግ በተለያዩ ተቋማት በተለያዩ መንገዶች ግንዛቤ መፈጠሩንም ባለሙያዋ ገልጸዋል።
ዘጋቢ፦ ዳግማዊ ተሰራ
ተጨማሪ መረጃዎችን
በቴሌግራም https://bit.ly/2wdQpiZ
ትዊተር https://bit.ly/37m6a4m
ዩቱዩብ https://bit.ly/38mpvDC ያገኛሉ፡፡