
ባሕር ዳር: ሚያዝያ 29/2017 ዓ.ም (አሚኮ) ወይዘሮ ፋጡማ አሕመድ ይባላሉ፡፡ በደቡብ ወሎ ዞን አልቡኮ ወረዳ 03 ቀበሌ ነዋሪ ናቸው፡፡ በመስኖ ልማት ሥራ ከተሰማሩ ከ10 ዓመታት በላይ እንደኾናቸው ተናግረዋል፡፡ ውኃው በአካባቢያችን ያለ ቢኾንም ለመስኖ ሥራ ተጠቅመነው አናውቅም ነበር ይላሉ፡፡ ከዓመታት ወዲህ ግን በግብርና ባለሙያዎች እገዛ በመስኖ ልማት ማኅበር በመታቀፍ በዓመት ሁለት እና ሦሥት ጊዜ ማምረት ችያለሁ ነው ያሉት፡፡
በሦሥት ጥማድ መሬት ካሮት፣ ቀይ ስር፣ ድንች፣ ጥቅል ጎመን እና ሌሎች አትክልቶችንም እንደሚያለሙ ነው የነገሩን፡፡ በዚህም የሙት ልጆቼን አስተምሬ ራሳቸውን አስችያለሁ፤ ያልጨረሱትን ደግሞ እያስተማርሁ ነው ብለዋል፡፡ የግብርና ባለሙያዎችን ለሚያደርጉላቸው ሙያዊ እገዛ እና ለሚሰጧቸው ምክረ ሀሳብ ምስጋናቸውን አቅርበዋል፡፡
የደቡብ ወሎ ዞን መስኖና ቆላማ አካባቢ ልማት መምሪያ ኀላፊ ተክሉ ጥላሁን በ2017 በጀት ዓመት አስራ ሰባት ነባር ፕሮጀክቶችን በመጨረስ ወደ ሥራ ለማስገባት ታቅዶ እየተሠራ መኾኑን ገልጸዋል። ከነዚህ ውስጥ አምስቱ በክልል ደረጃ የሚሠሩ ፕሮጀክቶች ናቸው ያሉት ኀላፊው አስራ ሁለቱ ፕሮጀክቶች በዞን እና ወረዳ ክትትል የሚሠሩ መኾናቸውን ተናግረዋል፡፡
በሴፍቲኔት ፕሮግራም ደግሞ አርባ ሦሥት ግንባታዎችን ለመሥራት ታስቦ ወደ ሥራ መገባቱን ገልጸዋል። ይህ ግንባታ ተጠናቅቆ ወደ ሥራ ሲገባ 1 ሺህ ሄክታር መሬት በላይ በማልማት 3 ሺህ 800 አርሶ አደሮችን ተጠቃሚ ያደርጋል ብለዋል፡፡
ባለፉት ዘጠኝ ወራት እንደ ክልል 114 ፕሮጀክቶች ማጠናቀቅ መቻሉን የአማራ የመስኖና ቆላማ አካባቢዎች ልማት ቢሮ አስታውቋል፡፡ 57 ነባር እና 53 አዲስ የመስኖ ፕሮጀክቶች የጥናት እና የዲዛይን ሥራ በማከናወን ወደ ሥራ መግባቱም ተመላክቷል።
የአማራ ክልል መስኖና ቆላማ አካባቢዎች ልማት ቢሮ ኀላፊ ኢንጂነር ዳኝነት ፈንታ (ዶ.ር) በበጀት ዓመቱ 82 ፕሮጀክቶች ለማጠናቀቅ ታቅዶ 114 ፕሮጀክቶችን የጥናትና ዲዛይን ሥራ ማጠናቀቅ እንደተቻለ ተናግረዋል።
ኾኖም በርከት ያሉ ፕሮጀክቶች በጸጥታው እና በተለያዩ ምክንያቶች ወደ ግንባታ አለመግባታቸውን ተናግረዋል፡፡ በቀጣይ ወደ ግንባታ ያልገቡ ፕሮጀክቶችን ወደ ሥራ ለማስገባት ሰፊ ጥረት እየተደረገ መኾኑንም ገልጸዋል፡፡
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን