
ወልድያ፡ ሚያዝያ 29/2017 ዓ.ም (አሚኮ) የክልል እና የዞን ከፍተኛ የሥራ ኀላፊዎች በሰሜን ወሎ ዞን በጉባላፍቶ ወረዳ ከበቅሎ ማነቂያ ከተማ 030 ቀበሌ ነዋሪዎች ጋር “የጥፋት እጆች እና መዘዞቹ” በሚል መሪ መልዕክት ሰላምን ለማረጋገጥ ምክክር አካሂደዋል። በመድረኩ የተገኙት የአማራ ክልል ምክትል ርእሰ መሥተዳድር አብዱ ሁሴን (ዶ.ር) ባለፈው አንድ ዓመት ከመንፈቅ ከመንግሥት ርቆ ከነበረ ሕዝብ ጋር በአካል በመገናኘታቸው ደስተኛ መኾናቸውን ገልጸዋል።
የሕዝቡን የሰላም ፍላጎት ለመመለስ መንግሥት ቁርጠኛ ነውም ብለዋል። ይሁን እንጂ ሰላም እንዲመጣ ከተፈለገ ነገሮችን በአስተውሎት ማየት እና የችግር ምንጩን በማወቅ መግባባት ያስፈልጋል ነው ያሉት። አሁን ያለውን ችግር ዕውነተኛ ምክንያት መረዳት እንደሚያስፈልግም አስረድተዋል። መንግሥት ችግሩን በሰላማዊ መንገድ ለመፍታት ሁሉንም አማራጭ ተጠቅሟል ያሉት ምክትል ርእሰ መሥተዳድሩ አሁንም በንግግር ችግሩን ለመፍታት ዝግጁ ነው ብለዋል።
በርካታ ወንድሞችም ወደ ሰላም መምጣታቸውን ነው ያብራሩት። ይሁን እንጂ አብዛኛው በጫካ ያለ ጽንፈኛ ቡድን ዘራፊ እና ወንጀለኛ በመኾኑ ሰላማዊ አማራጭን አይፈልግም ነው ያሉት። ሀገርን የሚጠብቀው አንድ መንግሥት እና አንድ የታጠቀ ኀይል ብቻ ስለመኾኑም ነው ምክትል ርእሰ መሥተዳድሩ የተናገሩት።
ሺፍታ የሀገር አዳኝ ሊኾን እንደማይችልም አብራርተዋል። ሀገርን ለማፍረስ ከባዕዳን ጋር የሚሠራ ቡድንን በትክክለኛ ስሙ መጥራት ተገቢ እንደኾነም ጠቁመዋል። የራሳችሁን ሰላም ራሳችሁ ጠብቁ፤ ልጆቻችሁንም ሸምግሉ ያሉት ምክትል ርእሰ መሥተዳድሩ መንግሥት ከሕዝቡ የተነሱ የመብራት፣ የውኃ፣ የቴሌ፣ የመንገድ እና መሰል የልማት ሥራዎችን መንግሥት በሂደት ይፈታል ነው ያሉት።
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን
