ባሕር ዳርን ለነዋሪዎቿ ምቹ ለማድረግ እየሠራ መኾኑን የባሕር ዳር ከተማ አስተዳደር አስታወቀ።

18

ባሕር ዳር: ሚያዝያ 29/2017 ዓ.ም (አሚኮ) የባሕር ዳር ከተማ አሥተዳደር ተቀዳሚ ምክትል ከንቲባ ጎሹ እንዳላማው እንዳሉት “ስማርት ባሕር ዳርን” ለመፍጠር ፕሮጀክት ጽሕፈት ቤት ተቋቁሞ እየተሠራ ነው። በቀጣይ ዓመታት ከተማዋን ጽዱ፣ ውብ፣ በዓለም አቀፍ ደረጃ የቱሪዝም እና የኢንቨስትመንት መዳረሻ ለማድረግ እየተሠራ መኾኑን ገልጸዋል።

ለዚህ ደግሞ የመጀመሪያውን የኮሪደር ልማት ማጠናቀቅ መቻሉ እና ሁለተኛውን የኮሪደር ልማት ደግሞ በቅርቡ ለመጀመር እየተደረገ ያለውን ዝግጅት በማሳያነት አቅርበዋል።

በከተማዋ ከ2011 እስከ 2014 ዓ.ም ባለው ጊዜ የተጀመሩ ከ20 እስከ 40 ሜትር ስፋት ያላቸው 21 ነጥብ 5 ኪሎ ሜትር የአስፋልት መንገድ እየተሠራ መኾኑንም ነው የገለጹት። ከዚህ ውስጥ ደግሞ 17 ኪሎ ሜትር የሚኾነው መንገድ በዚህ ዓመት እንደሚጠናቀቅ ገልጸዋል።

የከተማውን መሬት አሥተዳደር ማዘመን ደግሞ ሌላኛው ትኩረት የተሠጠው ጉዳይ ነው። በከተማዋ ይኖራል ተብሎ ከሚጠበቀው 100 ሺህ ፋይል ውስጥ እስከ አሁን የአራት ክፍለ ከተሞችን ማጠናቀቅ ተችሏል ብለዋል። ቀሪ የሁለት ክፍለ ከተሞችን ምዝገባ እስከ መጭው ግንቦት 30 ለማጠናቀቅ እየተሠራ መኾኑን ገልጸዋል።

የከተማዋን ደኅንነት ለማረጋገጥ ከሚያስፈልጉ 468 ካሜራዎች ውስጥ 75 ካሜራዎችን መግጠም መቻሉንም አንስተዋል። ካሜራዎቹ በ10 ኪሎ ሜትር ራዲዬስ መረጃ መሰብሰብ የሚችሉ መኾናቸው ተገልጿል።

አጠቃላይ የተቋማትን አገልግሎት አሠጣጥ እና አሠራር ለማዘመን በቴክኖሎጂ የማስተሳሰር ሥራ እየተሠራ መኾኑንም ነው ያነሱት።

የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን

Previous articleየሀገር መከላከያ ሠራዊት አባላት በደሴ ከተማ እየተሠራ ያለውን የኮሪደር ልማት ጎበኙ።
Next article“ሀገርን የሚጠብቀው አንድ መንግሥት እና አንድ የታጠቀ ኀይል ብቻ ነው” ምክትል ርእሰ መሥተዳድር አብዱ ሁሴን (ዶ.ር)