
ባሕር ዳር:ሚያዝያ 29/2017 ዓ.ም (አሚኮ) ርእሰ መሥተዳድር አረጋ ከበደ፣ የአማራ ክልል ብልጽግና ፓርቲ ቅርንጫፍ ጽሕፈት ቤት ኀላፊ ይርጋ ሲሳይ እና ሌሎችም የአማራ ክልል እና የጎንደር ከተማ አሥተዳደር መሪዎች በመገጭ መስኖ ግድብ ተገኝተው የፕሮጀክቱን የግንባታ እንቅስቃሴ ተመልክተዋል።
ርእሰ መሥተዳድር አረጋ ከበደ መገጭ የመስኖ ግድብ ከተጀመረ በርካታ ዓመታት ቢኾነውም ሳይጠናቀቅ የቆየ ነበር ብለዋል። ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ.ር) በሰጡት አቅጣጫ መሠረት ሥራው በአዲስ ተጀምሮ በፍጥነት እየተከናወነ ስለመኾኑም ተናግረዋል። ፕሮጀክቱ ከፍጥነት በተጨማሪ በጥራት እንዲከናወን ልዩ ቁጥጥር እና ክትትትል የሚደረግበት ስለመኾኑም ተናግረዋል።
ርእሰ መሥተዳድሩ በጉብኝቱ ወቅት እንዳሉት በጎንደር ዙሪያ የተለያዩ ትላልቅ የልማት ፕሮጀክቶች እየተሠሩ ነው። የመገጭ መስኖ ግድብ ፕሮጀክት አንዱ ሲኾን ሥራው ሲጠናቀቅ የአካባቢውን አርሶ አደሮች ምርታማነት ከፍ የሚደርግ ነው ብለዋል።
“የሰላም እና የልማት ተጠቃሚው፤ የጦርነትም ቀዳሚ ተጎጅው ሕዝብ ነው” ያሉት ርእሰ መሥተዳድሩ ነዋሪዎች ሰላማቸውን በመጠበቅ የልማቶችም ተባባሪ መኾን እንዳለባቸው መልዕክት አስተላልፈዋል።
ሕዝብን በቀጥታ ተጠቃሚ የሚያደርጉ በርካታ የልማት ሥራዎች በትኩረት እየተሠሩ ነው፤ እነዚህን የልማት ሥራዎች መደገፍ፣ መተባበር እና በጋራ ተጠቅሞ ኑሮን ማሻሻል ከሕዝቡ ይጠበቃል ብለዋል ርእሰ መሥተዳድሩ።
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን