
ባሕር ዳር: ሚያዝያ 29/2017 ዓ.ም (አሚኮ) የባሕር ዳር ከተማ አሥተዳደር ግብርና መምሪያ ለመኸር ሰብል ምርት የሚኾን የአፈር ማዳበሪያ ለአርሶ አደሮች እያሰራጨ መኾኑን ገልጿል።
የባሕርዳር ከተማ አሥተዳደር ግብርና መምሪያ ኀላፊ የሰውዘር ደመላሽ በዓመቱ 69 ሺህ 500 ኩንታል የአፈር ማደበሪያ ለማቅረብ መታቀዱን ገልጸዋል። እስካሁን 27 ሺህ ኩንታል የአፈር ማዳበሪያ መቅረቡንም ተናግረዋል። 6 ሺህ 500 ኩንታል ደግሞ ለአርሶ አደሮች መሰራጨቱን ገልጸዋል።
አርሶ አደሮች ግብዓቶችን ቀድመው እንዲወስዱ በንቅናቄ መድረክ ውይይት መደረጉን የገለጹት ኀላፊው በየአደረጃጀታቸው እየወሰዱ መኾኑን ተናግረዋል።
በከተማ አሥተዳደሩ በመስኖ እና በመኸር የሚለማ ሰፊ መሬት መኖሩንም ጠቅሰዋል። በመኸር የሚለማ 15 ሺህ 613 ሄክታር መሬት መኖሩንም ገልጸዋል።
በ2017/18 የምርት ዘመን 810 ሺህ 500 ኩንታል ምርት ለማግኘት ታቅዶ እየተሠራ መኾኑንም አመላክተዋል።
1 ሺህ 528 ኩንታል የበቆሎ ዘር ለማቅረብ መታቀዱን የገለጹት ኀላፊው 1 ሺህ 75 ኩንታል ቀርቦ 254 ኩንታል መሰራጨቱንም ገልጸዋል።
በዋጋ ጭማሪ ምክንያት ግንዛቤ እስኪፈጠር ድረስ ከመዘግየት በስተቀር አሁን ላይ የማዳበሪያ እጥረት አለመኖሩን ኀላፊው ገልጸዋል።
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን