“ቀጣናዊ የንግድ ትስስርን ማጠናከር ለተረጋጋ ኢኮኖሚ ግንባታ ወሳኝ ነው” አፈ ጉባኤ ታገሰ ጫፎ

21

አዲስ አበባ: ሚያዝያ 29/2017 ዓ.ም (አሚኮ) 6ኛው የኮሜሳ ሴቶች ፌዴሬሽን የቢዝነስ ኤግዚቪሽን በአዲስ አበባ መካሄድ ጀምራል።

በማስጀመሪያ መርሐ ግብሩ ላይ መልዕክት ያስተላለፉት የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አፈ ጉባኤ ታገሰ ጫፎ የሥርዓተ ፆታ እኩልነት አህጉር አቀፍ ትስስር የኢትዮጵያ የቆየ ፍላጎት እና በትኩረት የምትሠራበት ነው ብለዋል። ሥርዓተ ፆታን ከሴቶች ኢኮኖሚ አቅም ጋር ለማስተሳሰር የሚሠራው ኮሜሳ ከኢትዮጵያ ስትራቴጂ እና ፖሊሲ ጋር የሚዋደድ መኾኑን ገልጸዋል።

እነዚህን ተግባራት በትኩረት መሥራት አህጉር እና ቀጣና አቀፍ የኾነ የተረጋጋ ኢኮኖሚን ለመፍጠር ወሳኝ ነው ብለዋል። አፍሪካን እና ዓለምን እየፈተነ ያለው የኢኮኖሚ እና የአየር ንብረት ለውጥ ለመጋፈጥ አፍሪካውያን በአንድ ቆመው የኮሜሳ አይነት ተቋማትን በማጠናከር መሥራት ይገባቸዋል ብለዋል። ለዚህ ስኬት አጋዥ የኾነው የኮሜሳ ሴቶች የፌዴሬሽን ቢዝነስ ኤግዚቪሽንና ባዛር በይፋ ተከፍቷል ብለዋል።

የንግድና ቀጣናዊ ትስስር ሚኒስትር ካሳሁን ጎፌ (ዶ.ር) የኮሜሳ ሴቶች ፌዴሬሽን ቢዝነስ ማኅበር የሴቶችን ኢኮኖሚያዊ አቅም የሚያጎለብት መኾኑን ገልጸዋል። እንደ አህጉር የታሰበውን የነፃ ንግድ ቀጣናን ለመፍጠር ትልቅ አቅም እንዳለውም አስገንዝበዋል።

ኢትዮጵያ የኮሜሳ መሥራች እና አባል በመኾኗ ከሴቶች ፌዴሬሽን ቢዝነስ ማኅበር ጋር በቅንጅት በመሥራት የኢኮኖሚ ቀጣናዊ ትስስርን ለመፍጠር እገዛዋ ይቀጥላል ብለዋል።

የኮሜሳ ዋና ጸሐፊ ችለሲ ካፕዌፕዌ ኮሜሳ የፆታ እኩልነትን ለማረጋገጥ የሴቶችን ኢኮኖሚያዊ ተጠቃሚነት ማረጋገጥ ያስፈልጋል ብሎ ያምናል ብለዋል። ኮሜሳ ሴቶችን በኢኮኖሚ አቅማቸው እንዲፈረጥሙ ሁሉን አቀፍ ድጋፍ ያደርጋል ነው ያሉት።

የሴቶችን የኢኮኖሚ አቅም አህጉር አቀፍ ትስስርን መፍጠሪያ በማድረግ ከዘርፈ ብዙ ፋይዳ ጋር ማቀናጀት ይገባልም ብለዋል። የሥርዓተ ፆታ 2063 አጀንዳን ለማሳካት ይህ ከወሳኝ አማራጮች መካከል አንዱ መኾኑንም አመላክተዋል።

ዘጋቢ:- አዲሱ ዳዊት

የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን

Previous articleርእሰ መሥተዳድር አረጋ ከበደ በመገጭ መሥኖ ግድብ ፕሮጀክት ተገኝተው የሥራውን እንቅስቃሴ እየተመለከቱ ነው።
Next articleየአፈር ማዳበሪያ ለአርሶአደሮች እያሰራጨ መኾኑን የባሕር ዳር ከተማ አሥተዳደር ግብርና መምሪያ ገለጸ።