
ባሕር ዳር: ሚያዝያ 29/2017 ዓ.ም (አሚኮ) ከውጭ ይገባ የነበረውን ስማርት ፖል በሀገር ውስጥ በማምረት የውጭ ምንዛሬን እና ጊዜን ማዳን መቻሉንም ኢንዱስትሪው አስታውቋል።
የአማራ ብረታብረት ኢንዱስትሪ ዋና ሥራ አሥፈጻሚ ዘላለም በላይ በከተሞች በሚሠሩ የኮሪደር ልማት የመንገድ ዳርቻዎች ላይ የሚተከሉ ቢጫ ፍላዎር፣ ጥቁር እና ሲ ታይፕ (አይነት) “ስማርት ፖሎችን” ኢንዱስትሪው እያመረተ መኾኑን ገልጸዋል።
ፖሎቹ 18 የሚደርሱ ኤሌክትሪካል ፊቸሮችን የያዙ ናቸው። ከእነዚህ ውስጥ በትንሽ ኤሌክትሪክ ኀይል ብዙ አካባቢዎችን የሚሸፍኑ እና ለሰው እይታ የማይረብሹ መብራቶች ይገኙበታል። የትራፊክ እና ሌሎች እንቅስቃሴዎችን መቆጣጠር የሚያስችሉ የደኅንነት ካሜራዎች የተገጠመላቸው በመኾናቸው የትራፊክ ደኅንነት እና የአየር ጸባይ መረጃዎችን ማግኘት የሚያስችሉ ናቸው።
ገመድ አልባ እና የገመድ የሞባይል ቻርጅ፣ ወቅታዊ መረጃዎችን መስጠት የሚችሉ ዘመናዊ የዲጂታል ትዕይንተ መስኮቶች (ኤል ኢ.ዲ)፣ ችግሮችን በፍጥነት መፍታት የሚያስችሉ የአደጋ ጊዜ ማስጠንቀቂያዎች፣ የሙዚቃ ላውድ ስፒከሮች፣ አምስተኛው ትውልድ (5G) ኔትዎርክ የተገጠመላቸው መኾናቸውንም ገልጸዋል።
በአንድ መቆጣጠሪያ ማዕከል በኤሌክትሪክ ሴንሰር አማካይነት አየሩ ሲጨልም በራሱ ጊዜ የሚያበራ፣ ሲነጋ ደግሞ በራሱ ማጥፋት የሚያስችል ሥርዓትም አለው።
ዋና ሥራ አሥፈጻሚው እንዳሉት ስማርት ፖሎቹ እስከ 50 ዓመት አገልግሎት እንዲሰጡ ታስቦ የተዘጋጁ ናቸው። አገልግሎታቸውም እንደዘመኑ የቴክኖሎጂ አይነት መሳሪያውን በመግጠም አገልግሎት እንዲሰጡ የሚያስችሉ ናቸው ተብሏል።
ከውጭ ከሚገቡት ስማርት ፖሎች ከሚይዙት ፊቸር በመጠን ካልኾነ በስተቀር ተመሳሳይ መኾናቸውን ገልጸዋል። በሌሎች ከተሞችም ለማቅረብ እየተሠራ መኾኑን ገልጸዋል። በቀጣይ ለበርካታ ዜጎች የሥራ ዕድል የሚፈጥር መኾኑን ጠቅሰዋል።
የአማራ ብረታብረት ኢንዱስትሪ የባሕር ዳር ፍሌክሴብል ፋብሪካ ዋና ሥራ አሥኪያጅ ጥበቡ ደምስ እንደገለጹት ፋብሪካው ትኩረት ሰጥቶ ከሚሠራቸው ሥራዎች ውስጥ የውጭ ምንዛሬን በሀገር ውስጥ መተካት እና የቴክኖሎጂ ሽግግርን ማምጣት ነው። አሁን ላይ ከውጭ ይገባ የነበረውን ስማርት ፖል በሀገር ውስጥ በማምረት የውጭ ምንዛሬን እና ጊዜን ማዳን ተችሏል ብለዋል።
በኢንዱስትሪው ውስጥ የመገጣጠም እና ማጠናቀቅ ሥራ ክፍል ኀላፊ ይነበብ ታምሩ እንዳሉት በኢንዱስትሪው የተመረቱት እያንዳንዳቸው ስማርት ፖሎች የራሳቸው የኀይል መቆጣጠሪያ ሥርዓት ተዘጋጅቶላቸዋል። በሪሞት መታዘዝ የሚችሉ በመኾናቸው ሥራን የሚያቃልሉ መኾናቸውንም ገልጸዋል። በየትኛውም የአየር ንብረት አገልግሎት መስጠት የሚችሉ ፖሎችን በተለያየ መጠን ማምረት የሚያስችል አቅም መፍጠር መቻላቸውን አስታውቀዋል።
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን