
ሁመራ: ሚያዚያ 29/2017 ዓ.ም (አሚኮ) በአማራ ክልል ወልቃይት ጠገዴ ሰቲት ሁመራ ዞን የትራንስፖርት ዘርፉን የሚያሻሽሉ ተግባራት እየተከናወኑ መኾኑን የዞኑ ትራንስፖርት እና ሎጅስቲክስ ጽሕፈት ቤት አስታውቋል።
ጽሕፈት ቤቱ የዘጠኝ ወራት የዕቅድ አፈጻጸም ግምገማ እና የቀሪ ወራት ተግባራትን በተመለከተ የውይይት መድረክ አካሂዷል።
በመድረኩ ላይ የተገኙት የዞኑ ዋና አሥተዳዳሪ አሸተ ደምለው የትራንስፖርት ዘርፉን ከሕገ ወጥ ተግባራት አጥብቆ መከላከል እንደሚገባ ተናግረዋል። ሁሉም ተሽከርካሪዎች ሕጋዊ ሰነድ አሟልተው እንዲገኙ ማድረግም ያስፈልጋል ነው ያሉት።
የትራንስፖርት ባለሙያዎች እና የትራፊክ ፖሊሶች ተቀናጅተው በመሥራት ማኅበረሰቡን ከሕገ ወጥ ብዝበዛ ለመታደግ ቁርጠኛ መኾን ይጠበቅባቸዋል ብለዋል።
በተናጠል የሚደረግ የትኛውም ሥራ ውጤታማ ስለማያደርግ ቅንጅታዊ አሠራርን በማጠናከር የሕዝቡን ፍላጎት መሠረት ያደረገ አገልግሎት መስጠት የትራንስፖርት ዘርፉ ተቀዳሚ ተልዕኮ እንደኾነም ገልጸዋል።
ጽሕፈት ቤቱ ከመንገድ መምሪያ ተነጥሎ ራሱን የቻለው በቅርቡ መኾኑን የተናገሩት እና ራሱን በቻለባቸው ጥቂት ጊዚያትም ቢኾን መሥራት የሚጠበቅበትን ተግባራት በላቀ ደረጃ እያከናወነ ነው ያሉት የጽሕፈት ቤቱ ኀላፊ ለምለሙ ባየህ ናቸው።
ዘርፉን በቴክኖሎጅ እና በቁሳቁስ ለማሻሻል በርካታ ሥራዎች እየተከናወኑ መኾኑንም ተናግረዋል። የክልሉ ትራንስፖርት እና ሎጅስቲክስ ባለሥልጣን ከ60 ሚሊዮን ብር በላይ በሚገመት በጀት በቁሳቁስ መደገፉንም ገልጸዋል።
ትራንስፖርት ዘርፉ ራሱን ችሎ መደራጀት መቻሉ ለቀልጣፋ አገልግሎት ምቹ ኹኔታን የፈጠረ መኾኑን የመድረኩ ተሳታፊዎች ለአሚኮ ተናግረዋል።
የነዳጅ አቅርቦት ችግር፣ ትርፍ መጫን እና ከታሪፍ በላይ ማስከፈል በቀጣይ ትኩረት ተሰጥቶ ሊሠራባቸው የሚገቡ ጉዳዮች መኾናቸውን በመድረኩ በአጽንኦት የተነሱ ነጥቦች ናቸው።
ዘጋቢ: አምሳሉ አሞኘ
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን