
ባሕር ዳር፡ ግንቦት 12/2012 ዓ.ም (አብመድ) የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ዋና ፀሐፊ አንቶኒዮ ጉተሬዝ የታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብን ጉዳይ በቅርበት እየተከታተሉት መሆኑን አስታውቀዋል፡፡
የታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ኤሌክትሪክ ኃይል ማመንጫ ግድብ ግንባታን በተመለከተ ኢትዮጵያ፣ ሱዳንና ግብጽ ልዩነታቸውን ለማጥበብ ስለሄዱበት ርቀት የተናገሩት ዋና ፀሐፊው ሀገራቱ ቀሪ ጉዳዮቻቸውን በራሳቸው መፍታት እንዳለባቸውም አሳስበዋል፡፡
ሀገራቱ የጀመሩትን ጥረት በመቀጠል ልዩነታቸውን በሰላማዊና ሁሉንም ተጠቃሚ በሚያደርግ መልኩ መፍታት እንዳለባቸው ነው አንቶኒዮ ጉተሬዝ ያሳሰቡት፡፡
ሦስቱ ሀገራት እ.አ.አ በ2015 የሕዳሴ ግድቡን በተመለከተ ያደረጉትን ሥምምነት መለስ ብለው እንዲያጤኑትም ዋና ፀሐፊው አስታውሰዋል፡፡ ሥምምነቱ በጋራ ተጠቃሚነት ላይ የተመሠረተ ትብብር እንደሚያስፈልግ፣ ዓለም ዓቀፍ የወሰን ተሻጋሪ ወንዞች አጠቃቀምን የተመለከቱ መርሆዎችን ማክበር እንደሚገባ፣ ሦስቱ ሀገራት በግድቡ ግንባታ ላይ መተማመን መፍጠር እንደሚገባቸው የሚያትቱ ዐበይት ነጥቦችን የያዘ እንደነበርም ነው የተመድ ዋና ፀሐፊው ያስታወሱት፡፡ እነዚህን መርሆዎች መሠረት በማድረግ ወደተሻለ መግባባትና ሥምምነት መድረስም ተገቢ አማራጭ እንደሆነ ዋና ፀሐፊው ሐሳብ ሰጥተዋል፡፡
ምንጭ፡- የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት
በአስማማው በቀለ
ተጨማሪ መረጃዎችን
በቴሌግራም https://bit.ly/2wdQpiZ
ትዊተር https://bit.ly/37m6a4m
ዩቱዩብ https://bit.ly/38mpvDC ያገኛሉ፡፡