
ደሴ: ሚያዝያ 28/2017 ዓ.ም (አሚኮ) “ትብብር እና አጋርነት ለሁለንተናዊ ማኅበረሰብ ለውጥ” በሚል መሪ መልዕክት 24ኛው በአማራ ክልል የሚገኙ የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ፎረም በወሎ ዩኒቨርሲቲ አስተናጋጅነት እየተካሄደ ነው።
በፎረሙ በአማራ ክልል የሚገኙ የመንግሥት ከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ፕሬዝዳንቶች፣ የአካዳሚክና የምርምር ጉዳዮች ምክትል ፕሬዝዳንቶች እና የዩኒቨርስቲው የሥራ ኀላፊዎችን ጨምሮ ጥሪ የተደረገላቸው እንግዶች ተገኝተዋል።
ለፎረሙ ተሳታፊዎች የአማራ ክልል ርእሰ መሥተዳድር አረጋ ከበደ በቪዲዮ መልዕክት አስተላልፈዋል። በአማራ ክልል የሚገኙ የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ፎረም ከተመሠረተ ጊዜ አንስቶ በክልሉ በርካታ ተግባራትን ማከናወኑን ገልጸዋል ርእሰ መሥተዳድሩ።
“የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ማኅበረሰቡን የሚያሻሽሉ ጉዳዮች ላይ በትኩረት ሊሠሩ ይገባልም” ብለዋል። ዩኒቨርሲቲዎች ነፃ እና ገለልተኛ ኾነው ሥራዎችን እንዲያከናውኑም ነው በመልዕክታቸው የተናገሩት።
የወሎ ዩኒቨርሲቲ ፕሬዝዳንት አወል ሰይድ (ዶ.ር) ፎረሙ ዩኒቨርሲቲዎች ልምድ የምንለዋወጥበት ከመኾኑ ባሻገር በጋራ የምንሠራበትን እድል ፈጥሯል ብለዋል።
ፎረሙ በክልሉ የተለያዩ ዘርፎች ላይ የራሱን ድርሻ እየተወጣ ይገኛል ያሉት ፕሬዝዳንቱ በቴክኖሎጂ፣ በግብርና፣ በቱሪዝም፣ በዲጂታላይዜሽን እና ሌሎች ዘርፎች ላይ በትኩረት እየሠራ እንደሚገኝ ተናግረዋል።
የፎረሙ የቦርድ ሰብሳቢ እና የወልድያ ዩኒቨርሲቲ ፕሬዝዳንት አበበ ግርማ (ዶ.ር) ፎረሙ በ2005 ዓ.ም በሰባት ዩኒቨርሲቲዎች መመሥረቱን አስታውሰው በተለይ በኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝ እና በሰሜኑ ጦርነት ወቅት ሰብዓዊ ድጋፍ አድረጓል፣ በጦርነቱ በክልሉ የደረሰው ውድመት በባለሙያ እንዲጠና እና ድጋፎች እንዲደረጉ አስተባብሯል ነው ያሉት። ዩኒቨርሲቲዎች በእርሻ ሜካናይዜሽን እና በመስኖ እንዲሳተፉ፣ የዘር ብዜትን እንዲያግዙ እና የአፈር አሲዳማነትን ለመከላከል ሥራዎችን አከናውነዋልም ብለዋል።
በቀጣይም የፎረሙ አባል የኾኑ የመንግሥት ከፍተኛ የትምህርት ተቋማት በቴክኖሎጂ፣ በማኅበራዊ እና ሰብዓዊ ዘርፎች ላይ በትኩረት እንዲሠሩም አስገንዝበዋል።
ዘጋቢ:- ከድር አሊ
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን