
ባሕር ዳር: ሚያዝያ 28/2017 ዓ.ም (አሚኮ) አርሶ አደር ቁምላቸው ዳኛው በምዕራብ ደንቢያ ወረዳ ቸንከር ቂርቆስ ቀበሌ ነዋሪ ናቸው፡፡ የመስኖ ስንዴ በአንድ ሄክታር መሬት እንዳለሙ ተናግረዋል፡፡
አርሶ አደሩ አስፈላጊ ግብዓቶችን ተጠቅመው ከአንድ ሄክታር መሬት 36 ኩንታል ስንዴ ማምረት መቻላቸውን ተናግረዋል፡፡ በዚህም በፊት የመኸር ዝናብን በመጠበቅ አለማው ከነበረው ምርት የተሻለ ምርት ማግኘት ችያለሁ ነው ያሉት፡፡
በመስኖ ልማት ምርት የማምረት ሥራ ከተሰማራሁ ስድስት ዓመት ኾኖኛል ያሉት አርሶ አደር ቁምላቸው በፊት በዓመት አንዴ አመርት የነበረው አሁን በመስኖ ምርት በማምረት የተሻለ ኑሮን መኖር ችያለሁ ብለዋል፡፡
በዚህም አሁን ከምንሮበት ባለፈ ከተማ ላይ ቦታ ለመግዛት በቅቻለሁ፤ ለሚያስፈልገኝ ወጭ አልጨናነቅም ሲሉ የኑሮ ለውጣቸውን አስረድተውናል፡፡
በማዕከላዊ ጎንደር ዞን በዘንድሮው የመስኖ ስንዴ ልማት ከለማው ማሳ ላይ ከ652 ሺህ ኩንታል በላይ ምርት መሰብሰብ መቻሉን የማዕከላዊ ጎንደር ዞን ግብርና መምሪያ አስታውቋል፡፡
ዞኑ የበጋ መስኖ ስንዴ ልማትን ትኩረት ሰጥቶ እየሠራ ነው ያሉት የማዕከላዊ ጎንደር ዞን ግብርና መምሪያ የአትክልት እና ፍራፍሬ የመስኖ ውኃ አጠቃቀም ቡድን መሪ ሀውልቱ ታደሰ ናቸው፡፡ ቡድን መሪው የባለፈውን ዓመት የእቅድ መነሻ በማድረግ እና በማሳደግ በበጀት ዓመቱ 18 ሺህ ሄክታር መሬት ለማልማት በማቀድ ወደ ሥራ ተገብቷል ብለዋል፡፡
አዳዲስ የግብርና አሠራሮችን እና ቴክኖሎጂዎችን በመጠቀም እና ከዕቅድ በላይ ለማምረት በተደረገ ርብርብ ከእቅድ በላይ 19 ሺህ 200 ሄክታር መሬት ማልማት መቻሉንም ተናግረዋል፡፡ ይህም በመቶኛ ሲሰላ ከእቅዱ 106 በመቶ የሚኾነውን ማሳካት ተችሏል ነው ያሉት፡፡
በአጠቃላይ ከለማው መሬት 720 ሺህ ኩንታል ምርት ይጠበቃል፤ እስካሁን ቀድሞ የደረሰውን ሰብል በመሰብሰብ 652 ሺህ 800 ኩንታል የስንዴ ምርት ወደ ጎተራ ገብቷል ነው ያሉት፡፡ ይህም ቀደም ሲል በሄክታር ይገኝ የነበረውን 30 ኩንታል ምርት ወደ 34 ኩንታል ማሳደግ መቻሉን አስታውቀዋል፡፡
ከዚህ ጋር ተያይዞ ለአርሶ አደሮች እስከታች ድረስ የወረደ የክትትል እና ድጋፍ የማድረግ ሥራ በግብርና ባለሙያዎች ተደርጓል፤ በአመራሩም እስከታች ድረስ ተግባራቱን በመገምገም መመራት መቻሉ ከእቅድ በላይ ለማምረት እንዲቻል አድርጎታል ነው ያሉት፡፡
በአማራ ክልል የበጋ መስኖ ስንዴ ልማት 254 ሺህ ሄክታር መሬት በማልማት 9 ነጥብ 4 ሚሊዮን ኩንታል ምርት ለመሰብሰብ ታቅዶ ሲሠራ መቆየቱን የክልሉ ግብርና ቢሮ አስታውቋል፡፡
እስካሁን ባለው 207 ሺህ ሄክታር መሬት በዘር ተሸፍኗል፡፡ ከዚህም ወደ 5 ነጥብ 3 ሚሊዮን ኩንታል የመስኖ ስንዴ ምርት መሰብሰብ መቻሉን በግብርና ቢሮ የአትክልት እና ፍራፍሬ መስኖ ውኃ አጠቃቀም ዳይሬክተር ይበልጣል ወንድምነው ተናግረዋል፡፡
የበጋ መስኖ ስንዴን ለማልማት ትልልቅ የመስኖ መሰረተ ልማት ያለባቸው አካባቢዎችን በመምረጥ ሰፊ ሥራ እየተሠራ ነው ያሉት ዳይሬክተሩ ለቀጣይ ዓመት የዘንድሮ ዓመትን ተሞክሮ በመቀመር ፣ያጋጠሙ ችግሮችን በመለየት እና በማረም አዳዲስ የመስኖ ሥራዎች እንዲለሙ ለማድረግ የቅድመ ዝግጅት ሥራ ከወዲሁ መሥራት ይጠበቅብናል ብለዋል፡፡
ዘጋቢ፦ ሰናይት በየነ
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን