የሲራራ ንግድ ባለታሪኳ ጎንደር ዛሬም በዘመናዊ ንግድ ደምቃለች።

26

ባሕር ዳር: ሚያዝያ 28/2017 ዓ.ም (አሚኮ) ጎንደር ከአጼ ፋሲል ዘመን ጀምሮ ከቀይ ባሕር እስከ አውሮፓ በሚዘልቀው የሲራራ ንግድ ዋነኛ መተላለፊያ መስመር የነበረች ባለታሪክ ናት። አሁንም ቢኾን በዘመናዊ ንግዱ የተሰማሩ ሁሉ የሚያተርፉባት ከተማ ኾና ቀጥላለች።

በጎንደር በተለይም በቅባት እህሎች እና በቅመማ ቅመም ሙሉ ናት። የሁመራ ሰሊጥ እና የቆላድባ ጥቁር አዝሙድ ለጎንደር ገበያ ሲሳዮች ከኾኑት መካከል ጥቂቶቹ ናቸው።

በጎንደር ከተማ ከዛሬ ሚያዝያ 28 እስከ ግንቦት 15/2017 ዓ.ም የሚቆይ የንግድ ትርዒትና ባዛር ተዘጋጅቷል። የአማራ ክልል እና የጎንደር ከተማ አሥተዳደር ከፍተኛ መሪዎችም በቦታው ተገኝተው ባዛሩን ከፍተዋል። የገበያውን ሁኔታም ተዘዋውረው ተመልክተዋል።

የአማራ ክልል ብልጽግና ፓርቲ ቅርንጫፍ ጽሕፈት ቤት ኀላፊ ይርጋ ሲሳይ፣ የአማራ ክልል ሚሊሻ ጽሕፈት ቤት ኀላፊ አስቻለ አላምሬ፣ የአማራ ክልል ብልጽግና ፓርቲ ቅርንጫፍ ጽሕፈት ቤት የዲሞክራሲ ባሕል ግንባታ ዘርፍ ኀላፊ መስፍን አበጀ (ዶ.ር)፣ የጎንደር ከተማ አሥተዳደር ተቀዳሚ ምክትል ከንቲባ ቻላቸው ዳኘው እና ሌሎች መሪዎች ናቸው ባዛሩን የከፈቱት።

የጎንደር ከተማ አሥተዳደር ንግድ እና ገበያ ልማት መምሪያ ኀላፊ ቴዎድሮስ ፀጋዬ እንደገለጹት በንግድ ትርኢትና ባዛሩ ላይ አዲስ አበባን ጨምሮ በተለያዩ አካባቢዎች የሚገኙ አምራቾች እና አቅራቢዎች ሸቀጦቻቸውን ይዘው በጎንደር ተገኝተዋል። ይህ የንግድ ትርኢትና ባዛር በአይነቱ እና በመጠኑ ልዩ እና ከፍ ያለ ነው ብለዋል። የተለያዩ የግብርና፣ የኢንዱስትሪ እና የእንስሳት ተዋጽኦ ምርቶችም በስፋት እና በተመጣጣኝ ዋጋ የቀረቡበት መኾኑን ተናግረዋል።

ባዛሩ በተለይም የኑሮ ውድነት እና የዋጋ መናር ችግሩን ለማቃለል ሁነኛ ሚና ያለው መኾኑንም ጠቁመዋል። የኢንዱስትሪ ምርቶች ከአምራቾች በቀጥታ ቀርበዋል ያሉት ኀላፊው ቀደም ሲል በገበያ ላይ ካለው ዋጋም ከ30 እስከ 50 በመቶ ቅናሽ እንዳለ ገልጸዋል።

በባዛሩ ከ115 በላይ አምራቾች እየተሳተፉ ነው፤ የሀገር ውጭ አምራቾችም እየተሳተፉ ነው ብለዋል። የንግድ ትርኢትና ባዛሩ በርካታ አምራቾችን እና ሸማቾችን ያገናኘ፣ የጎንደርን ሰላማዊ የግብይት እና የሥራ ማዕከልነትም ያረጋገጠ መኾኑን አንስተዋል።

የጎንደር ከተማ አሥተዳደር የዘርፍ ማኅበራት ምክር ቤት ፕሬዝዳንት ሚሊዮን መለሰ አምራቾችን ከሸማቾች በቀጥታ በማገናኘት ገበያው እንዲረጋጋ እየተሠራ መኾኑን ገልጸዋል። ከሌሎች ከተሞች ማኅበራት ጋር በመነጋገር ምርቶችን እንደ የአስፈላጊነቱ ከቦታ ቦታ በማጓጓዝ በተለይም በዝቅተኛ የኑሮ ደረጃ ላይ የሚገኙ የኅብረተሰብ ክፍሎችን ተጠቃሚ እያደረግን ነው ብለዋል።

ከአሚኮ ጋር ቆይታ ያደረጉት ምርት አቅራቢዎች ከተለያዩ ቦታዎች ወደ ጎንደር ተጉዘው መምጣታቸውን ነግረውናል። ጎንደር የሰላም እና የሥራ ቦታ ናት፤ ምርቶቻችንን በተመጣጣኝ ዋጋ እየሸጥን ነው ብለዋል።

ሸማቾችም በንግድ ትርኢትና ባዛሩ ከመደበኛው ገበያ በቀነሰ ዋጋ የተለያዩ ምርቶችን እየሸመቱ መኾኑን ተናግረዋል።

የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን

Previous article“መሪዎች የችግር ወቅት እና የአዲስ ተስፋ አመራር ብቃት ልትሰንቁ ይገባል” ምክትል ርእሰ መሥተዳድር አብዱ ሁሴን (ዶ.ር)
Next article“በአማራ ክልል በመስኖ ስንዴ ከ5 ሚሊዮን ኩንታል በላይ ምርት መሰብሰብ ተችሏል” የክልሉ ግብርና ቢሮ