ለዘላቂ ሰላም መረጋገጥ የበኩላቸውን ድርሻ እንደሚወጡ የቻግኒ ከተማ ነዋሪዎች ተናገሩ።

14

እንጅባራ: ሚያዝያ 28/2017 ዓ.ም (አሚኮ) የክልል እና የዞን ከፍተኛ የሥራ ኀላፊዎች በአዊ ብሔረሰብ አሥተዳደር ከቻግኒ ከተማ ነዋሪዎች ጋር ” የጥፋት እጆች እና መዘዞቹ ” በሚል መሪ መልዕክት በወቅታዊ የሰላም እና ጸጥታ ጉዳይ ላይ ያተኮረ ሕዝባዊ ውይይት አካሂደዋል።

የከተማዋ ነዋሪዎች በክልሉ የተፈጠረው ቀውስ ሰብዓዊ እና ቁሳዊ ውድመት ማድረሱን ገልጸዋል። በዜጎች መካከል መተማመን እንዲጠፋ እና ሥርዓት አልበኝነት እንዲነግስ ማድረጉንም ተናግረዋል።

የክልሉ ሕዝብ ላይ እየደረሰ ያለው በደል መቋጫውን እንዲያገኝ ከመንግሥት ጎን ኾነው እንደሚሠሩም ነዋሪዎቹ ገልጸዋል።

የንጹሕ መጠጥ ውኃ አቅርቦት፣ የወጣቶች የሥራ ዕድል ፈጠራ፣ የመኖሪያ ቤት መሥሪያ ቦታ አቅርቦት፣ የመብራት ሰብስቴሽን እና ሌሎች ጥያቄዎች እንዲፈቱም ነዋሪዎቹ ጠይቀዋል።

የአማራ ሚዲያ ኮርፖሬሽን የዋና ሥራ አሥፈጻሚ አማካሪ ግዛቸው ሙሉነህ መድረኩ ኅብረተሰቡ በክልሉ የተፈጠረው ቀውስ ያደረሰውን ጉዳት በውል እንዲረዳ እና ከችግሩ መውጫ መንገዶች ላይ የበኩሉን ድርሻ እንዲወጣ የሚያስችል መኾኑን ተናግረዋል።

መንግሥት ከኅብረተሰቡ ለሚነሱ የልማት እና የመልካም አሥተዳደር ጥያቄዎች በሂደት እንዲፈቱ በቁርጠኝነት እየሠራ ነውም ብለዋል።

የቻግኒ ከተማ ሰላም የእያንዳንዱ ነዋሪ የሰላም ፍላጎት እና የተግባር ውጤት ነው ያሉት አቶ ግዛቸው ኅብረተሰቡ የቀደመ አብሮነቱን በማጠናከር ሰላሙን ማጽናት እንዳለበት አስገንዝበዋል።

የቻግኒ ከተማ አሥተዳደር ተቀዳሚ ምክትል ከንቲባ ይበልጣል ሰይድ ኅብረተሰቡ ለሰላም ባለው ጽኑ ፍላጎት እና በጸጥታ አካላት እና በመሪዎች ቁርጠኝነት የከተማዋ ሰላም በጥሩ ሁኔታ ላይ መኾኑን ተናግረዋል።

ከተማ አሥተዳደሩ ከነዋሪዎች የሚነሱ የልማት፣ የመልካም አሥተዳደር እና የፍትሐዊ ተጠቃሚነት ጥያቄዎች ምላሽ እንዲያገኙ እየሠራ መኾኑንም ገልጸዋል።

ዘጋቢ: ሳሙኤል አማረ

የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!

https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን

Previous articleሁሉም ለሰላም በቁርጠኝነት መሥራት ይጠበቅበታል።
Next article“ፋይዳ ለኢትዮጵያ” በሚል መሪ መልዕክት የሩጫ ውድድር ሊካሄድ ነው።