
ባሕር ዳር: ሚያዝያ 28/2017 ዓ.ም (አሚኮ) በሰሜን ወሎ ዞን በላስታ ወረዳ እና በላሊበላ ከተማ አሥተዳደር ”የጥፋት እጆችና መዘዞቹ” በሚል መሪ መልዕክት ከመንግሥት ሠራተኞች ጋር ውይይት ተካሂዷል።
በውይይቱ መልዕክት ያስተላለፉት የሰሜን ወሎ ዞን ኢንዱስትሪ እና ኢንቨስትመንት መምሪያ ኀላፊ ሞላ ደሱ በተፈጠረው የጸጥታ ችግር ምክንያት በሚፈለገው ደረጃ ልማታችንን ማስቀጠል፣ ሕዝባችንን ማገልገል ሳንችል ቆይተናል ነው ያሉት።
ላስታ ላሊበላ በዓለም ታዋቂ የኾነ የሀገር ውስጥ እና የውጭ ሀገር ጎብኝዎች ለመጎብኘት የሚጓጉለት ቦታ ነው ያሉት ኀላፊው በተፈጠረው የፀጥታ ችግር ምክንያት ጎብኝዎች በተፈለገው ልክ የማይመጡበት፣ ሆቴሎች እና ሌሎች ተቋሞቻችን ሥራ የማይሠሩበት ሁኔታ ተፈጥሯል ነው ያሉት።
የመንግሥት ሠራተኞች ወደ ቀበሌ ወርደው ለሕዝቡ አገልግሎት እንዳይሰጡ እና የተጀመሩ የልማት ሥራዎች በሚፈለገው ደረጃ እንዳይጠናቀቁ እንቅፋት ፈጥሮ እንደቆየ ነው የተናገሩት።
የሰላምን አስፈላጊነት ተገንዝበን ለሰላም በቁርጠኝነት መሥራት ይጠበቅብናል ብለዋል። ሰላም በማጣታችን ምንክያት በማኅበራዊ ልማት፣ በኢኮኖሚ እና በመልካም አሥተዳደር በሰባዊ ቁሳችን ጭምር ከፍተኛ ጉዳት ደርሷል ነው ያሉት።
ከዚህ ችግር ለመውጣት የመንግሥት ሠራተኞች የበኩላቸውን አስተዋጽኦ እንዲያደርጉ ጠይቀዋል።
የላሊበላ ከተማ አሥተዳደር ተቀዳሚ ምክትል ከንቲባ ወንድምነው ወዳጅ በተፈጠረው የፀጥታ ችግር ምክንያት ከፍተኛ የሆነ ሰብዓዊና ኢኮኖሚያዊ ችግር ደርሷል ነው ያሉት።
የደረሰውን ሰባዊ እና ቁሳዊ ኪሳራ ተረድተን እያንዳንዳችን ከዚህ አስከፊ ችግር ለመውጣት እና ዘላቂ ሰላምን ለማረጋገጥ የድርሻችን መወጣት አለብን ብለዋል።
የላስታ ወረዳ ዋና አሥተዳዳሪ ኢንጅነር ለዓለም ብርሃኑ ሰላም ከአንድ ወገን ብቻ የሚመጣ ባለመሆኑ ሁሉም ለሰላም የድርሻውን መወጣት እንደሚገባው ገልጸዋል።
ከሰሜን ወሎ ዞን ኮሙዩኒኬሽን የተገኘው መረጃ እንደሚያመላክተው ክልሉ ከገጠመው ዘርፈ ብዙ ችግር ለመውጣት በትኩረት መሥራት ይጠበቅብናል ብለዋል።
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን