
ባሕር ዳር: ሚያዝያ 28/2017 ዓ.ም (አሚኮ) ባሕር ዳር “ውብ ከተማ ነች” ሲባል በውበቷ የማይስማማ አንድም ሰው አይገኝም፡፡ ይልቁንም ከባሕር ዳር ስም ጋር ተያይዞ የሚነሳው የጫት ጉዳይ፤ ስሟን እንዳያጠለሸው ሥጋቴ ላቅ ያለ ነው፡፡
ከባሕር ዳር ከተማ ተነስታችሁ በየትኛውም አቅጣጫ ስትጓዙ በትናንሽ መንደሮች ሳይቀር “የባሕር ዳር ጫት እዚህ ይገኛል” የሚለውን ማስታወቂያ በማንበባችሁ ምን ያህላችሁ እንደ እኔ እንደምትበሽቁ ጥያቄውን ለናንተው ትቼዋለሁ፡፡
ባሕር ዳር ጣናን የመሰለ ሐይቅ፣ ዓባይን የመሰለ የወገቧ መቀነት የኾነ ወንዝ፣ ጥላ እና ጌጥ የኾኗት ዘንባባዎች፣ ተበልቶ የማይጠገብ ዓሳ እያሏት፣ ከስሟ ጋር አብሮ የሚጠራው “የባሕር ዳር ጫት” የተፈጥሮ ጸጋዎቿንም ኾነ ሰው ሠራሽ ውበቷን ከል የሚያለብስባት ወይም ጥላሸት የሚቀባባት ኾኗል፡፡
“ስም ይወጣ ከቤት ይከተል ጎረቤት” እንዲሉ ኾኖ በባሕር ዳር ዙሪያ በሚገኙ የአርሶ አደሮች መሬት ላይ የሚበቅለው ጫት “የባሕር ዳር ጫት” እየተባለ በአራቱም የሀገሪቱ አቅጣጫዎች ይሰራጫል፤ ይሸጣል፡፡ ባሕር ዳርም ዙሪያ እና መሀሏን ባስዋባት ዘንባባዋ ሳትጠራ ከከተማዋ ቅርብ እርቀት በሚመረት ጫት ስሟን በየአቅጣጫው እያስጠራች ትገኛለች፡፡
በደርግ ጊዜ ነው አሉ ሀገራችን የምትከተለው የሶሻሊስት ሥርዓትን ስለነበረ በየስብሰባ አዳራሹ ሌኒን እንዳለው፣ ማርክስ እንዳለው፣ ኤንግልስ እንዳለው… እየተባለ ሶሻሊስታዊ ሃሳብ ይቀነቀናል፡፡ ከስብሰባ ውጭም ራሳቸውን ፖለቲከኛ ነን ብለው የፈረጁ ሰዎች አዋቂነታቸውን ለሌሎች ለማስረዳት ሲፈልጉ ሌኒን እንዳለው፣ ማርክስ እንዳለው፣ ኤንግልስ እንዳለው …እያሉ ምንጭ ጠቅሰው ያወራሉ፡፡
አንድ አዛውንት ደግሞ በሄዱበት አቅጣጫ እና በሬዲዮ ሳይቀር ሌኒን እንዳለው፣ ማርክስ እንዳለው እና ኤንግልስ እንዳለው የሚሉ ነገሮችን ደጋግመው ሲሰሙ ”መውለድስ ካልቀረ እንደዚያ እንዳለው እንደ ተባለው ሰው ነበረ፤ የእሱ ልጆች በየስብሰባው፣ በየታክሲው እና በራዲዮናችን ሳይቀር እከሌ እንዳለው እየተባሉ ይጠራሉ“ ሲሉ ሶሻሊስት የፈጠራቸውን እንዳለው አብዝተው አደነቁ አሉ፡፡
ይህንን አባባል እዚህ ትዝብቴ መካከል የሰነቀርኩት በየሀገሩ ”የባሕር ዳር ጫት“ እየተባለ የባሕር ዳርን ስም የሚያስጠራው ጫት እንደ አቶ እንዳለው የሌለ በመኾኑ እና በባሕር ዳር ከተማ ውስጥ ጫት ስለማይመረት ነው፡፡
ጫት አደንዛዥ ዕጽ ከመኾኑ ጋር ተያይዞ ምጣኔ ሃብታዊም ኾነ ማኅበራዊ ቀውስ የሚያስከትል ተክል እንጂ ለጤና ተስማሚ የኾነ አትክልት ወይም ሌላ አይደለም፡፡ ባሕር ዳር በዚህ በሚነወር ተክል ስሟ መታወቁም ቢኾን በጥሩ መነገር አይኖርበትም፡፡
የጎጃም ጤፍ፣ የፎገራ ሩዝ፣ የዘጌ ቡና፣ የደቅ ማንጎ፣ የደብረ ሲና ቆሎ፣ የሐይቅ ብርቱካን እና ሌላም እየተባለ ስሙ በጥሩ የሚነሳው የአማራ ክልል ለዋና ከተማዋ በተሰጣት ”የባሕር ዳር ጫት“ ስያሜ ምክንያት ጥሩዎቹ ስዕሎቻችን እንዳይደበዝዙ ስጋት አለኝ፡፡
ወደ ባሕር ዳር ሲመጡም ኾነ ከባሕር ዳር ተነስተው ወደ ተለያዩ አቅጣጫዎች በየብስ ሲጓዙ የሚያዩት ”የባሕር ዳር ጫት“ ማስታወቂያ ስህተት እንደኾነ እኔ እማኝ ነኝ፡፡ ባይኾን ”የባሕር ዳር ዓሳ“ ሲባል ሰምተው ከኾነ እሱ እውነተኛ የከተማዋ መገለጫ ሊኾን ይችላል፡፡
የባሕር ዳር ዓሳ ቀረሶ፣ አምባዛ እና ሌላም ስያሜን ይዞ ከጣና ሐይቅ እና ከዓባይ ወንዝ እየወጣ የብዙዎቻችንን አምሮት ቆርጧል፡፡ ወደ አዲስ አበባ እና ሌሎች ከተሞች እየተላከም ባሕር ዳርን በጥሩ ስሟ አስተዋውቋታል፡፡ ”የባሕር ዳር ጫት“ የሚባለው ግን የከተማዋ መታወቂያ መኾን የለበትም፤ አይደለምም፡፡
የንግድ ስም የንግድ ሥራ ፈቃድ የተሰጣቸው ነጋዴዎች የንግድ መደብሮቻቸውን የሚሰይሟቸው የንግድ ስሞች ስለመመዝገቡ የሚሰጥ የባለቤትነት ማስረጃ ስለመኾኑ ከንግድ ሚኒስቴር ድህረ-ገጽ ያገኘሁት መረጃ ይጠቁማል፡፡ በዚህ አሠራር መሠረት ለባሕር ዳር ጫት ማን የሚባለው የንግድ ተቋም ስያሜ ወስዶ ነው የባሕር ዳር ጫት እየተባለ የሚጠራው ብለን መጠየቅም እንችላለን፡፡
የባሕር ዳር ከተማ አሥተዳደር የባሕር ዳር ጫት በሚለው የወጣ የንግድ ፈቃድ እስከሌለ ድረስ የከተማየን ስም ከጫት ጋር የሚያነሱ ነጋዴዎችን በሕግ እጠይቃለሁ ማለትም የሚችል ይመስለኛል፡፡ ደግሞም ይሄ ጥያቄ መነሳቱ ተገቢ ነውም ብዬ አምናለሁ፡፡ እናንተስ?
ዘጋቢ፡- እሱባለው ይርጋ
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን