
አዲስ አበባ: ሚያዝያ 28/2017 ዓ.ም (አሚኮ) ከግንቦት 4/2017 ዓ.ም እስከ ከግንቦት 7/2017 ዓ.ም በቱሪዝም ሚኒስቴር እና በዩኔስኮ ትብብር የሚካሄደውን የጅኦ ቱሪዝም እና የጅኦ ፓርክ ወርክሾፕን በተመለከተ የቱሪዝም ሚኒስትር ሸላማዊት ካሳ መግለጫ ሰጥተዋል።
ወርክ ሾፑ “የዩኔስኮ ዓለም አቀፍ ጅኦፓርኮች እና ጅኦቱሪዝም ለዘላቂ ልማት ያላቸው ሚና”በሚል መሪ መልዕክት ቀጣናዊ መድረክ ኾኖ ይካሄዳል፡፡ እንደ ኢትዮጵያ ሁሉ በርካታ የምሥራቅ አፍሪካ ሀገራት አስገራሚ የጅኦሎጂ ሀብቶች እንዳሏቸው ሚኒስትሯ ተናግረዋል። እነዚህን ሀብቶች በአግባቡ ለይቶ፣ ጠብቆ እና ለዘላቂ ማኅበራዊ እና ኢኮኖሚያዊ ጥቅሞች ለማዋል በጉዳዩ ላይ በቂ ግንዛቤ መፍጠር እና በባለድርሻ አካላት መካከል ቅንጅት መፍጠር ተገቢ መኾኑን አንስተዋል።
ወርክሾፑ በጅኦፓርክ እና በጅኦ ቱሪዝም ላይ የባለድርሻ አካላትን ግንዛቤ በማሳደግ እና አቅማቸውን በማጠናከር በኢትዮጵያ እና በሌሎች የምሥራቅ አፍሪካ ሀገራት የግሎባል ጅኦፓርክስ ፕሮጀክቶችን ለማስጀመር የሚያስችል መነቃቃት መፍጠር አንዲቻል የተዘጋጀ ነው ብለዋል።
ባለድርሻ አካላት በጅኦሎጂካል ቅርሶች ፋይዳ በቂ ግንዛቤ እንዲኖራቸው እና እነዚህን ሀብቶች በአግባቡ በመለየት፣ በመጠበቅ እና በማልማት ተጠቃሚነትን ለማረጋገጥ በሚችሉበት ሁኔታ ዕውቀት እንዲጨብጡ ማድረግ እንደሚገባ ነው ያስረዱት።
ጅኦሎጂካል ቅርሶችን እንዴት መለየት፣ ማጥናት፣ መጠበቅ፣ ማልማት የሚቻልባቸውን ዘዴዎች እና አሠራሮችን በተመለከተ ዕውቀት እና ግንዛቤ መፍጠርም ሌሎች የሁነቱ ተጨማሪ ዓላማዎች ናቸው ብለዋል። “በተወሰኑ የቱሪዝም ዘርፎች ላይ የተንጠለጠለውን የቱሪዝም አካሄድ በመቀየር አማራጭ ዘርፎችን ማስፋት ተገቢ ነው” ብለዋል በመግለጫቸው።
በዚህ ሁነት ከ10 ሀገራት የሚመጡ የዘርፉ ኤክስፐርቶች እና የሥራ ኀላፊዎች ይታደማሉ ነው የተባለው። በኢትዮጵያ የተመረጡ የጅኦሎጂ ቅርሶች በተለይም የጢያ ትክል ድንጋዮች፣ የመልካ ኩንጥሬ ባልጭት የአርኪዮሎጂ ስፍራ እና ሌሎች በእነዚህ አካባቢ የሚገኙ ስፍራዎች ይጎበኛሉ ተብሎ እንደሚጠበቅ ሚኒስትሯ ጠቁመዋል።
ዘጋቢ፦ አዲሱ ዳዊት
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን