በአሜሪካና ካናዳ የሚኖሩ ተወላጆች ለወልድያ ሆስፒታል ድጋፍ አደረጉ፡፡

171

ባሕር ዳር፡ ግንቦት 12/2012 ዓ.ም (አብመድ) በአሜሪካና ካናዳ የሚኖሩ የወልድያና አካባቢው ተወላጆች የኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝን ምክንያት በማድረግ ለወልደያ ጠቅላላ ሆስፒታል የሕክምና ቁሳቁስ ድጋፍ አድርገዋል፡፡

ድጋፉ ስድስት አምቡላንስ መኪና ላይ የሚገጠም የኦክስጅን መስጫ፣ 60 ባለ 42 ሊትርና 40 ጌጅ ሲሊንደር ከነኦክስጅኑ ናቸው፡፡ ድጋፉ በገንዘብ ሲተመን ከ400 ሺህ ብር በላይ መሆኑ ታውቋል፡፡ ንብረቱ በወልድያ ከተማ አስተዳደር በሚኖሩ በጎ ፈቃደኛ ወጣቶች ግዥ ተፈጽሞ ለሆስፒታሉ ርክክብ ተደርጓል፡፡

የወልድያ ጠቅላላ ሆስፒታል ሜዲካል ዳይሬክተር ተስፋየ ሙላው (ዶክተር) በሆስፒታሉ ያለው የጌጅ መጠን አነስተኛ በመሆኑ በአንድ ጊዜ 10 ታካሚዎችን ሲያስተናግድ እንደነበረ ገልጸው አሁን በተደረገው ድጋፍ 50 በኦክስጅን የተደገፈ ሕክምና መስጠት እንደሚያስችል ጠቁመዋል፡፡

ድጋፉ የሆስፒታሉን የሕክምና ቁሳቁስ እጥረት ከማቃለሉም ባሻገር አሁን ለተከሰተው የኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝ ሕክምና ለመስጠት ከፍተኛ አስተዋጽኦ እንዳለው አስረድተዋል፡፡

የወልድያ ከተማ አስተዳደር ከንቲባ ሙሃመድ ያሲን ደግሞ በአሜሪካና ካናዳ የሚኖሩ የወልድያና አካባቢው ተወላጆች ራሳቸውም በኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝ ከፍተኛ ጫና ውስጥ ሆነው ለወገናቸው በማሰብ ላደረጉት ድጋፍ በከተማ አስተዳደሩ ሥም ምሥጋና አቅርበዋል፡፡

ሌሎቹ የአካባቢው ተወላጆችና ባለሀብቶች መሰል ድጋፍ ቢያደርጉ ወረርሽኙን ለመግታት ትልቅ አቅም እንደሚሆንና ችግሮችን ለማቃለል አስተዋጽኦ እንደሚያበረክት በመግለጽም ጥሪ ተደርጓል፡፡

ዘጋቢ፡- ዋሴ ባየ -ከወልድያ

ተጨማሪ መረጃዎችን
በቴሌግራም https://bit.ly/2wdQpiZ
ትዊተር https://bit.ly/37m6a4m
ዩቱዩብ https://bit.ly/38mpvDC ያገኛሉ፡፡

Previous articleህንድና ባንግላዴሽ በከባድ ጎርፍና የመሬት መንሸራተት ስጋት ላይ ወድቀዋል፡፡
Next articleሀገራቱ የሕዳሴ ግድቡን ጉዳይ በራሳቸው እንዲፈቱ የተመድ ዋና ፀሐፊ አሳሰቡ፡፡