የእናቶች በጤና ተቋማት የመውለድ ምጣኔን ለማሳደግ እየሠራ መኾኑን የአማራ ክልል ጤና ቢሮ አስታወቀ።

19

ባሕር ዳር: ሚያዝያ 28/2017 ዓ.ም (አሚኮ) የዓለም ጤና ድርጅት መረጃ እንደሚያሳየው በዓለም ሕይዎታቸው ካለፈው እናቶች ውስጥ 75 በመቶ የሚኾኑት ከፍተኛ የደም መፍሰስ በተለይም ደግሞ ከወሊድ በኋላ የሚያጋጥም ደም መፍሰስ፣ በእርግዝና ወቅት የሚያጋጥም የደም ግፊት፣ “ኢንፌክሽን”፣ ውሥብሥብ የኾነ ወሊድ እና ደኅንነቱ ያልተጠበቀ ውርጃ ዋና ምክንያቶች ኾነው ተቀምጠዋል።

አንድ እናት እስከ ስምንት ጊዜ በጤና ተቋማት ክትትል ማድረግ እንዳለባት ድርጅቱ እንደመለኪያ ቢያስቀምጥም በአማራ ክልል በተፈጠረው የጸጥታ ችግር የአንዲት እናት የአራት ጊዜ ክትትል ምጣኔ እንኳ ከ64 በመቶ አለማለፉን የጤና ቢሮ መረጃ ያሳያል። የአዊ ብሔረሰብ አሥተዳደር ባለፉት ዘጠኝ ወራት የእናቶችን ሞት ለመቀነስ ከእርግዝና ጀምሮ በጤና ተቋማት አገልግሎት እንዲያገኙ ሲሠራ ቆይቷል።

የአዊ ብሔረሰብ አሥተዳደር ጤና መምሪያ ኀላፊ አየለ አልማው እንዳሉት በብሔረሰብ አሥተዳደሩ ገጠራማ አካባቢዎች በሚገኙ ሁሉም ጤና ጣብያዎች የእናቶች ማቆያ በማዘጋጀት የክትትል ሥራ ሲሠራ ቆይቷል። ይሁን እንጅ በከተሞች አካባቢ ለጤና ተቋማት ካላቸው ቅርበት አኳያ በእናቶች ማቆያ የመገልገሉ ባሕል ዝቅተኛ መኾኑን ገልጸዋል።

ከዚህ በፊት በብሔረሰብ አሥተዳደሩ የእናቶች በጤና ተቋማት የመውለድ ምጣኔ እስከ 70 በመቶ ነበር ነው ያሉት። በ2017 በጀት ዓመት ዘጠኝ ወራት በጤና ተቋማት ይወልዳሉ ተብሎ ከታቀዱት እናቶች በጤና ተቋማት የወለዱት 60 በመቶ ብቻ ናቸው። የጤና ተቋማት በደረጃው መሠረት ማኅበረሰቡን ባማከለ መንገድ አለመስፋፋት እና በአንዳንድ አካባቢዎች የተከሰተው የጸጥታ ሁኔታ በጤና ተቋማት ክትትል ማድረግ የሚገባቸው እናቶች አገልግሎቱን እንዳያገኙ አድርጓል ብለዋል።

የአማራ ክልል ጤና ቢሮ ምክትል ኀላፊ ገስጥ ጥላሁን በክልሉ ባለፉት ዘጠኝ ወራት ከእርግዝና ጋር በተያያዘ ሊከሰት የሚችለውን ሞት ለመቀነስ ነፍሰጡሮችን ቀድሞ በመለየት ግንዛቤ የመፍጠር እና የክትትል ሥራ ሢሠራ እንደቆየም አስገንዝበዋል። ለትራንስፖርት ምቹ ባልኾነባቸው እና ከጤና ተቋማት ርቀት ባላቸው አካባቢዎች የሚገኙ ነፍሰ ጡሮችን ደግሞ በእናቶች ማቆያ አገልግሎት እንዲያገኙ ተደርጓል ብለዋል።

በ2017 ዓ.ም 82 በመቶ ነፍሰጡር እናቶችን በጤና ተቋማት እንዲወልዱ ለማድረግ እየተሠራ ቢገኝም በበጀት ዓመቱ የእናቶች በጤና ተቋማት የመውለድ ምጣኔ ከ60 በመቶ የበለጠ አለመኾኑ ተገልጿል። ለዚህ ደግሞ የጸጥታ ችግር ዋነኛ ምክንያት ተደርጎ ተቀምጧል። ይሁን እንጅ በአምቡላንስ አጠቃቀም እና በመንገዶች መስተካከል ምክንያት አሁን ላይ የእናቶች በጤና ተቋማት የመውለድ ምጣኔ ከመጀመሪያው ሩብ ዓመት ከነበረው 40 በመቶ ወደ 60 በመቶ ማሳደግ ተችሏል ብለዋል።

ዘጋቢ፦ ዳግማዊ ተሠራ

የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!

https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን

Previous articleየአሠሪ እና ሠራተኛ መብትና ግዴታ እስከ ምን ድረስ ነው?
Next articleከፍተኛ መሪዎች በጎንደር ከተማ የተስፋ ብርሃን የምገባ ማዕከልን ጎበኙ።