ከፍተኛ የሥራ ኀላፊዎች በጎንደር ከተማ ትምህርት ቤቶች የተማሪዎችን ምገባ መርሐ ግብር እየጎበኙ ነው።

17

ባሕር ዳር: ሚያዝያ 28/2017 ዓ.ም (አሚኮ) በጉብኝቱ የአማራ ክልል ብልጽግና ፓርቲ ቅርንጫፍ ጽሕፈት ቤት ኀላፊ ይርጋ ሲሳይ፣ የአማራ ክልል ሚሊሻ ጽሕፈት ቤት ኀላፊ አስቻለ አላምሬ፣ የአማራ ክልል ብልጽግና ፓርቲ ቅርንጫፍ ጽሕፈት ቤት የፖለቲካ ባሕል ግንባታ ዘርፍ ኀላፊ መስፍን አበጀ (ዶ.ር)፣ የጎንደር ከተማ አሥተዳደር ተቀዳሚ ምክትል ከንቲባ ቻላቸው ዳኘው እና ሌሎችም መሪዎች ተገኝተዋል።

መሪዎች ከተመለከቷቸው ትምህርት ቤቶች ውስጥ ኅብረት አንደኛ ደረጃ ሙሉ ሳይክል ትምህርት ቤት እና መሠረት አንደኛ እና መካከለኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ይገኙበታል። በእነዚህ ትምህርት ቤቶች ከ2016 ዓ.ም ጀምሮ ሙሉ የምገባ መርሐ ግብር እየተካሄደ እንደሚገኝ ርእሳነ መምሕራኑ ለመሪዎች ገልጸዋል።

በኅብረት አንደኛ ደረጃ ሙሉ ሳይክል ትምህርት ቤት ለ230 አጸደ ሕጻናት ተማሪዎች የወተት እና ዳቦ ምገባ ያለማቋረጥ እየተካሄደ ነው ተብሏል። በመሠረት አንደኛ እና መካከለኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ደግሞ 560 የአጸደ ሕጻናት ተማሪዎች የመርሐ ግብሩ ተጠቃሚ ናቸው።

የምገባ መርሐ ግብሩ ለእለት ቁርስ እንኳን ተቸግረው ቤት የቀሩ ተማሪዎችን ወደ ትምህርት ገበታ ያመጣ እና በትምህርት አቀባበላቸው ላይም ተጨባጭ ለውጥ እየተመዘገበበት ያለ መኾኑንም ተገልጿል።

በጎንደር ከተማ አሥተዳደር በ11 ትምህርት ቤቶች ውስጥ በአጠቃላይ 3 ሺህ 26 ተማሪዎች በከተማው በጀት የምገባ መርሐ ግብር ተጠቃሚ መኾናቸውም ተመላክቷል።

የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን

Previous article“የሕዝባችን ቀዳሚ ምርጫው ሰላም፤ ፍላጎቱም ልማት ነው” ርእሰ መሥተዳድር አረጋ ከበደ
Next articleየአሠሪ እና ሠራተኛ መብትና ግዴታ እስከ ምን ድረስ ነው?